ዜና
ስብከት

                                                                                             በመ/ር ሽፈራው እንደሻው
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከቀደምት አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዷ እንደመሆኗ መጠን የተመሰረተችበት መሠረተ እምነት፤የተለያዩ ውሳኔዎችንና ሥርዓቶችን ያሳለፈችበትና የደነገገችበት ቀኖና እንዲሁም ከቀደሙት አባቶች የተረከበችው መንፈሳዊ ትውፊቷ  ምልከታዋን የሚያሰፉ  የማንነት መነጽሮቿ ናቸው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚሰጡ መንፈሳዊ አገልግሎቶች ተደራሽነታቸውን ለማስፋትና የአማንያኑን መንፈሳዊ ህይወት ለመገንባት በዓላትንና አፅዋማትን አስመርኩዞ ዘመኑን የሚዋጅና ወቅቱንም የሚዘክር አስተምህሮ በማዘጋጀት፤ተከታዮቿንም በመመገብና በመጠበቅ እነሆ ሽህ ዓመታትን አስቆጥራለች፤አሁንም በማገልገል ላይ ትገኛለች፡፡ከሰባቱ አፅዋማት አንዱ የሆነው በፀደይና በበጋው ወቅቶች  መካከል የሚታሰበውንም ጾመ-ነቢያት ወይም ጾመ-ስብከት በሳምንቱ እሁዶች በመከፋፈል መጻጉዕ፤ስብከት፤ብርሃን፤ ኖላዊ…… የሚል  አስተምህሮዊ ስያሜ በመስጠትና ለእያንዳንዳቸውም ከወንጌሉና ከመልዕክታቱ እንዲሁም ከመዝሙሩ ጋር የሚጎዳኝ ትምህርት በማዘጋጀት የመመገቡን ሥራ ተያይዛዋለች፡፡ከታህሳስ ሰባት እስከ ታህሳስ አስራ ሶስት ባሉት ተካታታይ ቀናት ውስጥ ስብከት በሚል መጠሪያ የተሰየመ ሲሆን  የነቢያት የዘመናት ጩኸት የተደመጠበት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ክፍል የሚዳሰስበት ጊዜ ነው፡፡ነቢያት ከተለያየ የኑሮ ደረጃና አስተሳሰብ፤እንዲሁም በተላያየ ወቅት የተጠሩ ከእግዚአብሔር የሆነውን ቅዱስ ቃል በመቀበልና ለህዝቡም በማስተላለፍ ረገድ ድልድይ ሆነው ያገለገሉ የእግዚአብሔር  አግለጋዮች ናቸው፡፡በውድቀት ውስጥ ለነበረውና አቅጣጫውን ለሳተው የሰው ልጅ አቅጣጫ በማሳየትና የብርሃን ተስፋ በመርጨት ትልቁን ድርሻ የወሰዱ አፈ-እግዚአብሔር እንደነበሩም የቅዱሳት መጻህፍት ምስክርነት በቂ ነው፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ ሽክም ለከበደውና ከኃጢአት አረንቋ ውስጥ ለወደቀው የሰው ልጅ አርያም የሚደርስ የድርስልን ጥሪ በማሰማትም ከእነርሱ በላይ የጮኸ፤ከእነርሱ በላይ የመሲሁን መምጣት የናፈቀ፤ስለነጻነት የደከመ፤እንዳልነበረና ምን ያክል እንደተጨነቁ ፈኑ እዴከ እምአርያም አቤቱ ክንድህን ከአርያም ላክ (መዝ 143፡7) በማለት የእግዚአብሔር ክንድ የሆነውን መሲህ እንዲመጣላቸው ያሳዩት መናፈቅ በቂ ማስረጃ ነው፡፡እውነት ነው፤በጨለማ ውስጥ ለነበረ ህዝብ የብርሃን ጥያቄውን የሚመልስ ብርሃን፤ብቸኝነት ለወረረው አማኑኤል የመሆን መልስ፤ጽድቅ ለተጠማ መንጋ እውነተኛና ጽድቅ ሆኖ በሰማያዊ መቅደስ የሚታይ የፅድቅ መልስ፤ሽክም ለከበደውና የአሳርፈን ጥያቄ ለሚያጎርፍ ተሸካሚ ከነሸክማችሁ ወደኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ በማለት በቀራንዮ በደልና መተላለፍን የሚሸከምና የኃጢአትን ደመወዝ የሚከፍል መልሳዊ መድኃኒት ያስፈልግ ነበር፡፡በመጨረሻም የጥያቄዎች ሁሉ መልስ በማድረግ እግዚአብሔር አብ የተወደደና አንድያ ልጁን ለኃጢአተኛው ዓለም ገፀ-በረከት አደረጎ ሰጠ፡፡    
በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 1፤44- ፍጻሜ  የሚገኘው  መጽሐፍ  ቅዱሳዊ ክፍል በዘመኑ ፍጻሜ ከሴት የተወለደው መሲህ (ገላ 4፡4) መገለጡን በሚገባ እንድንገነዘብ ይረዳናል፡፡ለበርካታ ጥያቄዎች አምላከዊ መልስ ሆኖ ከዙፋኑ የወረደው መሲህ በምድር ላይ ለሚመሠርተው መንግስት የራሱን ዜጎች በሚጠራበት ጊዜ የመጀመሪያዎቹ እድምተኞች ሁለቱ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት እንደነበሩም ክፍሉ ያረጋግጥልናል፡፡የጥሪው ድምፅ እየተቀጣጠለ፤ፍጥነቱም እየጨመረ በመሄዱ የመሲሁ ጉዞም ወደገሊላ አቀና፡፡ተጨማሪ ደቀ መዛሙርትንም ቀላቀለ፤ፊሊጶስ የተባለው የቤተሳይዳው ሰው ጥሪ ያደረገለትንና ያከበረውን አካል፤ለናትናኤል ሲያስረዳ ሙሴ በህግ መጻህፍት፤ነቢያት በነቢያት መጻህፈት ስለእርሱ የጻፉለትን አገኘነው፤እርሱም የዮሴፍ ልጅ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነው፡፡(ዮሐ 1፡45) በማለት ነበር፡፡ተጋባዡ ናትናኤልም መሲሁን ከማየት ይልቅ ስለከተማዋ ደሃራዊ ታሪክ ለመተረክ ቢሞክርም በተገናኘበት ቅጽበት መምህር ሆይ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤አንተ የእስራኤል ንጉስ ነህ (ዮሐ 1፡49) የሚል የልጅነት ሥልጣኑንና የመሲህነቱን ትርጓሜ ከመመስከር ግን አልተቆጠበም፡፡መሲሁ  ሙሴ  በህግ መጻህፍት የመሰከረለት፤ነቢያት በትንቢት የተናገሩለት፤ሽክም የከበደው ህዝብ ያሳርፈን ጥሪ ያቀረበለትና የዘመናት ጥያቄ መልስ ሆኖ የመጣው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡መሲሁ  ክርስቶስ እግዚአብሔር አብ ሥራውን ሁሉ የሰራበት፤ኃጢአትን የደመሰሰበትና  መርገምን የቆረጠበት ቀኝ ክንዱ ነው፡መሲሁ ክርስቶስ የምድራችን ሰላም የተረጋገጠበት ሰላም የሰላም አለቃ ኃያል አምላክ ነው፡፡መሲሁ ክርስቶስ የዓለም ኃጢአትና በደል በአልጋ ላይ ለጣለው የኃጢአት በሽተኛና የአልጋ ቁራኛ  ለሆነ ሁሉ እውነተኛና ፍቱን መድኃኒት እርሱ ነው፡፡ነቢያት ስለዚህ መሲህ ብዙ ትንቢት ተናገሩ፤ብዙ ጻፉ፤የሕይወት መስዋእትነትም ከፈሉ፤ከፍተኛ የጥሪ ድምጽም አሰሙ፤የጥሪውን ድምፅ በሚገባ ያደመጠው፤ትንቢታቸውን በከንፈራቸው ያስቀመጠው፡የባህርይ አባቱ እግዚአብሔር አብ የተወደደውንና አንድያ ልጁን ለኃጢአተኛው ዓለም ምርጥ የኃጢአት ዋጋ አድርጎ ሰጠን፤በእኛና በእግዚአብሔር መካከል የተቆረጠውን ድልድይ እንደገና በመስራት በድጋሚ አገናኘን፤ከሞት ሊያውም ከዘላለም ሞት ሕይወታችንን ታደገው፡፡
ውድ አንባብያን ሆይ ለጥያቄዎቻችን ሁሉ መልስ ሆኖ ከሰማይ የመጣውን፤ከአባቱ ጋር የነበረውን መተካከል እንደክብር ሳይቆጥር ከክብር በታች የወረደውን፤ለሞት ሊያውም የመስቀል ሞት እንኳን የታዘዘውን፤ነጻ አውጭውንና አዳኙን መሲህ ቤተ ክርስቲያን  የአካሏ ተቆጣጣሪና መሪ በማድረግ ተቀብለዋለች ደግሞም እየሰበከችው ትገኛለች ልትሰብከውም ይገባታል፡፡ እኛም በተሰጠን የሕይወት ቆይታ የተሰቀለውንና መድኃኒት የሆነውን ልጁን በማመንና የክርስትና ልምምድ ውስጥ በመግባት በሕይወታችን፤፤በትዳርችን፤በኑሯችን፤በምድራችንና በዓለማችን እንስበከው፤ስለተሸከመልንም የበደል ሽክም እናመስግነው፤ለጥሪያችንም እንኑር፤የተቀደሰና ክርስቲያናዊ ሕይወትን እንድንገፋ፤በሞቱ ያከበረንንና በሰማያዊ ሥፍራ ያስቀመጠንን ክርስቶስን እየሰበክንና ስለእርሱም እየመሰከርን እንድንኖር የእግዚአብሔር ጸጋ ይርዳን፡ እያልኩ ኢሳ 64 እና ዮሐ 1፡44-ፍጻሜ ያለውን ክፍል ታነቡኝ ዘንድ ግብዣዬ ነው፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሄር፡፡

 
የታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም ዓመታዊ በዓልና የገዳሙን መቶኛ ዓመት የምሥረታ በዓል በታላቅ ድምቀት አከበረ

                                                                                          በመ/ር ሣህሉ አድማሱ

beata2

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም በዓተ ቤተ መቅደስ በዓል እና የዳግማዊ አፄ ምኒልክን የዕረፍት መታሰቢያ በዓል በየዓመቱ ታህሳስ  3 ቀን ሲአከብር መቆየቱ ይታወቃል፡፡ በዘንድሮውም ዓመት ታህሳስ 3 ቀን 2010 ዓ.ም ባከበረው የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም በዓተ ቤተ መቅደስ  እና የዳግማዊ አፄ ምኒልክ የዕረፍት መታሰቢያ በዓል በተጨማሪ ገዳሙ የተመሠረተበትን የመቶኛ ዓመት በዓል  ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፣ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣
ብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያ ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መምህር ጎይቶኦም ያይኑ፣ የገዳማትና የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና በርካታ ምዕመናን በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተከብሯል፡፡ ገዳሙ በተመሠረተበት ዕለት ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ (ወስመጥምቀተ አስካለማርያም) ከሕንጻው አናት ላይ በመቆም ታላቅ ዕልልታ በማሰማት ደስታዋን  እንደገለጸች ታውቋል፡፡
የዘንድሮውን በዓል አከባበር ለየት የሚያደርገው ነጋሪት ተጎስሟል፡፡ ዕንቢልታ ተነፍቷል፣ በገና ተደርድሯል፤ የቅዱስ ያሬድ ድርሰት የሆነው እና በየዓመቱ  በሊቃውንቱ በዜማ፣ በዝማሜ እና በወረብ ሲቀርብ የቆየው ንዒ ርግብ… ስምኪ ወለትዬ አስካለ ማርያም የሚለው ያሬዳዊ ቃለ እግዚአብሔር  መሳጭ በሆነ ጣዕመ ዜማ ተዘምሯል፡፡
የበበት ንግሥተ ነገሥታት አስካለ ማርያም በአፉሃ… የሚል ያሬዳዊ ግሥ በገዳሙ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በወረብ ተዘምሯል፡፡
ከዚያም የገዳሙ ሰበካ ጉባዔ ምክትል ሊቀ መንበር የሕንጻውን የምሥረታ በዓል መቶኛ ዓመት በዓል አስመልክተው ባቀረቡት ሪፖርት ሕንጻው ከዕድሜ ብዛት የተነሳ እየፈረሰ መሆኑን እና እድሳቱ በአስቸኳይ መታደስ እንዳለበት ሲገልፁ የገዳሙ ሀብት በደርግ ሥርዓት መወሰዱ፣ ያካባቢው ምዕመናን በመልሶ ማልማት አካባቢውን በመልቀቃቸው፣ ለአብነት ት/ቤቱ መታደስ የገንዘብ እጥረት ማጋጠሙን አብራርተዋል፡፡
ስለ ሕንጻው ቅድመ እድሳት የገዳሙ ኮሚቴ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሥነ ሕንጻ ምሁራን ጋር ውይይት ማካሄዱንም በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም በአንድ የሥነ ሕንጻ ምሁር ስለ ህንጻው የመፍረስ አደጋ ሙያዊ አስተያየት ተሰጥቷል፡፡ ጥገናውም በልዩ ትኩረት የሚካሄድ ነው ተብሏል፡፡
ሕንጻው የሀገር ቅርስ በመሆኑ እና በሕንጻው ውስጥ የነገሥታት አጽም የሚገኝበት በመሆኑ ሁሉም የበኩሉን ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባው የሥነ ሕንጻ ምሁሩ መልእክታቸው አስተላልፈዋል፡፡
ከዚህ በመቀጠል ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የቀሌም ወለጋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በዓሉን አስተመልክተው በሰጡት ትምህርት የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ወላጆች ሐና እና ኢያቄም በንጽሕና በቅድስና በመጸለያቸው ዓለምን የምታስታርቅ ልጅ ወለዱ፡፡ እመቤታችንም ኑሮዋን ከመላእክት ጋር አደረገች፡፡
እግዚአብሔርን በቤተ መቅደስ በመኖር አገለገለች በማለት የታሪኩን ቅደም ተከተል በተገቢው መንገድ በመዘርዘር ሰፋ ያለ ትምህርት አስተምረዋል፡፡ በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ አቅድም አእኩተቶ (ሮሜ.8) በሚል ርዕስ ጀምረው በዚህ በተቀደሰው እና ታሪካዊ በሆነው አውደምሕረት የተገኘነው ሁላችንም እግዚአብሔር ይባርከን ይቀድሰን፡፡ በዓሉ ታላቅ በዓል ነው፡፡ ይህን በዓል፤ በደመቀ ሁኔታ አክብረነዋል፡፡
ቤተ መቅደስ በተሠራበት ቦታ ሁሉ እግዚአብሔርን ስናመሰግን እንኖራለን፡፡
ኢትዮጵያ የሃይማኖት ሀገር ናት፡፡ ከአባቶቻችን የወረስነውን የቀና ሃይማኖታችንን አፅንተን ልንጠብቅ ይገባናል፡፡ ህልውናውን አምላክነቱን አዳኝነቱን መጋቢነቱን እንድናውቅ ያደረግን አምላክ አነሣሥቶን ነው ወደ ቤተ መቅደስ የመጣነው፡፡ ሥፍር ቁጥር  የሌለው ሕዝብ ያላት ሀገር ኢትዮጵያ ናት፡፡ ይህም መታደል ነው፡፡ ኢትዮጵያ በዓልም የተደነቀች ሀገር ናት፡፡ ቱሪስቱ የሚመጣው ወደ ኢትዮጵያ ነው፡፡ የዛሬ በዓል የሚታወቀው እመቤታችን ወደ ቤተ መቅደስ የገባችበት ዕለት በመሆኑ ነው፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ሥጋ ለብሶ ዓለምን ለማዳን ስላሰበ  ከእመቤታችን ተወለደ በማለት ሰፋ ያለ ትምህርትና አባታዊ ቃለ ምዕዳን በመስጠትና በዕድሜ ብዛት ለመፍረስ የተቃረበውን ሕንጻ ጥገና እንዲደረግ አባታዊ ጥሪ በማስተላለፍ የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል፡፡

 
መፃጉእ

                                                             በመ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የራሷ የሆነ ሥርዓተ አምልኮና ደንብ ያላት ቤተ-ክርስቲያን ናት፡፡ ሥርዓተ አምልኮዋን ከምትፈፅምባቸው መንፈሳዊ መሳሪያዎች መካከል አንዱ ፆም እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በአዋጅ ከደነገገቻቸው አፅዋማት መካከል አሁን እየፆምን የምንገኘው የነቢያት ፆም አንዱ ነው፡፡ ይህ ፆም ነቢያት የጌታን መወለድ በታላቅ ፍቅርና በጉጉት ሲጠባበቁ የፆሙት ፆም ነው፡፡ ሲጠበቅ የነበረውም የዓለም መድኃኒት የሆነው መሲህ ጊዜው ሲደርስ ተወልዷል፡፡ ቤተ-ክርስቲያኒቷ ይህ ፆም እንዲ ፆም ያወጀችው ነቢያት  ፆመው በረከት አግኝተውበታና  አማኞችም ቢፆሙት በረከት ያገኙበታል የሚለውን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ ቤተክርስቲያኒቷ ይህንን ፆም ከህዳር 14 እስከ  ታኅሳስ 29  ባሉት ቀናት  ውስጥ እንዲፆም በቀኖናዋ አውጃለች፡፡ በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ግን በ28 ፆሙ ይፈታል፡፡ በእነዚህ ወራት ውስጥ ያሉት እሁዶች የራሳቸው የሆነ ስያሜ አላቸው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ከህዳር 27 እስከ ታኅሳስ 3 ቀናት ባለው ጊዜ ውስጥ የዋለ እሁድ መፃጉዕ በመባል ይታወቃል፡፡ የነገው እሁድ  በቀን አንድ ስለዋለ መፃጉዕ ይባላል ማለት ነው፡፡ በዚህ ዕለትም ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዕውርን ያበራበት፣ ድውን የፈወሰበት፣ ተስፋ የሌላቸውን ተስፋ የሰጠበት ዕለት እንደሆነ በቤተክርስቲያን እየታሰበ ይዘመራል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በቅዳሴግዜ የሚነበቡትን የመፅሐፍ ቅዱስ ክፍሎች  የሚያወጣው ግፃሚ/ማውጫ  ተብሎ  የሚጠራው መፅሐፍ በዕለቱ  እንዲሰበክ ያዘዘውን ምስባክና እንዲነበብ ያዘዘውን ወንጌል መሠረት አድርገን ሰፋ ባለ መልኩ በቅደም ተከተል በትንታኔ እንመለከታቸዋለን፡፡
መዝ 4÷2-3 “ደቂቀእጓለ እመሕያው እስከ ማዕዜኑ ታከብዱ ልበክሙ ለምንት ታፈቅሩ ከንቶ ወተሐሱ ሐሰተ አእምሩ ከመ ተሰብሐ እግዚአብሔር በፃድቁ”
ትርጉም “እናንተ የሰው ልጆች እስከ መቼ ድረስ  ልባችሁን ታከብዳላችሁ? ከንቱ ነገርን  ለምን ትወድዳላችሁ?ሐሰትንም ለምን ትሻላችሁ? እግዚአብሔር በፃድቁ እንደተገለጠ እወቁ”
መፃጉእ ማለት በሽተኛ፣በደዌ የተመታ፣ ሕሙም ማለት ነው፡፡መጽሐፍ ቅዱስን መሰረት አድርገን ስንነጋገር በሽታ የመጣው ከአዳምና ከሔዋን ውደቀት ጀምሮ ነው፡፡ ይህም በሽታ በኃጢአት ምክንያት ወደ ዓለም እንደገባ እንረዳለን፡፡ አዳም እና ሔዋን ከወደቁ በኋላ ወዲያውኑ ፍርሃትና ስቃይ ተሰማቸው ዘፍ 3÷10፡16፡17፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ መገለጫውን በፍርሃት እና በስቃይ የጀመረው በሽታየተለያየ ይዘት አለው፡፡ መንፈሳዊ ዕውርነት፣ የአዕምሮ በሽታ፣ ልዩ ልዩ የሰውነት በሽታ፣ ልዩ ልዩ የውስጥ ደዌ በሽታ፣ ወዘተ….ብለን ልንዘረዝረው እንችላለን፡፡ በሌላ መልኩ ለእግዚአብሔር አለመታዘዝ ተወዳዳሪ የሌለው ትልቁ የዓላማችን በሽታ ነው፡፡ ከላይ ያነሳነው መዝ 4÷2-3 ላይ የሚገኘው የእግዚአብሔር  ቃል ይህንን እውነት ያረጋግጥልና፡፡ በዚያን ዘመን የነበሩት  የሰው ልጆች ልባቸውን ምን ያህል እንዳከበዱ፣ ከንቱ ነገርን እንደወደዱና ሐሰትንም የሚሹ  መሆናቸውን ይገልፃል፡፡ የሰው ልጅ ልቡን ካከበደ አስከፊ በሆነው የአለመታዘዝ በሽታ ውስጥ እተሰቃየ ነው፡፡ከእግዚአብሔርእየራቀ እና ሕይወትን እያጣ ይሄዳል፡፡
ልቡን ያከበደ ሰው ሀሰቡ  ደንድኗል ማለት ነው፡፡ ልባቸውን የሚያከብዱ በልባቸው ለእግዚአብሔር ስፍራ የላቸውም፡፡ ይህ ማለት በሃሳባቸው ውስጥ እግዚአብሔርን አያነግሱም፡፡ ስለዚህ ይህ ደግሞ አደገኛ አስከፊ በሽታ ቢባል ያንሰዋል እንጂ አይበዛበትም፡፡ እግዚአብሔርን ያላነገሱ ልቦች ውጤት ደግሞ ከንቱ  የሆነውን ነገር ነው በልባቸው የሚያነግሱት፡፡ በከንቱ ተሞልቶ መመላለስ  የሐሰት መንገድ ነው፡፡ ለዚህ ነው ቃሉ “እናንተ የሰው ልጆች እስከመቼ ድረስ ልባችሁን ታከብዳላችሁ? ከንቱ ነገርን ለምን ትወድዳላችሁ? ሐሰትንም ለምን ትሻላችሁ?እግዚአብሔር በፃድቁ እንደተገለጠ እወቁ” የሚለን፡፡ ዛሬም ቢሆን ብዙዎች ለእግዚአብሔር ቃል ጊዜ የለንም፣ እግዚአብሔርን አንሰማም የሚሉ ነገር ግን በልባቸው ኃላፊና ጠፊ የሆነው የዚህ ዓለም ጣጣ የነገሰባቸው፣በልባቸው ለእግዚአብሔር  ስፍራ የሌላቸው፣ ሁሌም ጊዚያዊ ለሆነው ነገር ብቻ የሚሯሯጡ አሉ፡፡ ይህ ግን ውጤቱ ዜሮ ነው፡፡ የሚሻለውና አማራጭ የሌለው ጉዳይ ወደ እግዚአብሔር መመለስ ነው፡፡ እግዚአብሔር የጨለመን ልቦና በራሱ ቃል ማብራት ይችልበታል፡፡ ልብ የእግዚአብሔርን ቃል ለመቀበል በመንፈስ ቅዱስ በኩል በፀጋው መረሰረስ አለበት፡፡ ንፁህ ልብ በእግዚአብሔር ዘንድ እጅግ ተወዳጅ ነው፡፡ ማቴ 5÷8 “ልበ ንፁሖች በፁዓን ናቸው እግዚአብሔርን ያዩታልና”  ነው የተባለው፡፡ እግዚአብሔርን ለማየት የሀብት ብዛት፣ ገንዘብ፣ ዝና፣ ስልጣን፣ የትምህርት ደረጃ፣ የጤና ጉዳይ፣ የዕድሜ ጉዳይ መስፈርት ሆኖ አልተቀመጠም፡፡ መስፈርቱ ንፅህ ልብን መያዝ ነው፡፡
 በዕለቱ የሚነበበው ወንጌል በዮሐንስ ወንጌል ምዕ 9÷1 እስከ ፍፃሜ ያለው የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቃል ሲሆን ይህ ምዕራፍ 41 ቁጥሮች ሲኖሩት አንድ ዕውር ሆኖ ስለተወለደ ሰው፣  ይህ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ከዕውርን እንደተላቀቀ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ሰው ለምን በሰንበት ፈወሰው ብለው ፈረሳውያን ፀብ ማንሳታቸው፣ የፈረሳውያንን መንፈሳዊ ዕውርነት፣ የተፈወሰው ሰው በፈረሳውያን ከምኩራብ መባረር እና የተባረረውን ሰው ክርስቶስ በውጭ ሆኖ መቀበሉ የምዕራፍ ዋና ዋና ሃሳቦች ናቸው፡፡ ጌታችን መድኃኒታእን ኢየሱስ ክርስቶስ ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደበት ትልቁ ዓላማ የሰው ልጆችን ለማዳንና የዘላለም ሕይወትን ለመሰጠት ነው፡፡ 1 ዮሐ 4÷14 “እኛም አይተናል አባትም ልጁን የዓለም መድኃኒት ሊሆን እንደላከው እንመሰክራለን” ይላል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የሥጋም የነፍስም መድኃኒት ነው፡፡ ደግሞም ለዓለም ሁሉ የሚበቃ መድኃኒት ነው፡፡ ኢየሱስ ማለት አዳኝ፣ መድኃኒት ማለት ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማንኛውንም ዐይነት በሽታና ደዌ መፈወስ ይችላል፡፡ በዚህ ባነሳነው ምዕራፍ ላይ ከልደቱ ጀምሮ ዕውር ሆኖ የተወለደውን ሰው ክርስቶስ እንደፈወሰው እናነባለን፡፡ በእግርጥ ደቀ መዛሙርቱ እንደጠየቁትና ኢየሱስ ክርስቶስም እንደመለሰው ይህ  ሰው ዕውር ሆኖ  የተወለደው የእግዚአብሔር ስራ በእርሱ እንዲገለጥ ነው እንጂ እርሱ ወይም ወላጆቹ ኃጢአት ሰርተው እንዳልሆነ ገልጿል፡፡
ጠቅለል ባለ መልኩ መፃጉእ በሚለው ርእስ ካነሳነው ትምህርት የሚከተሉትን እውነቶች እንረዳለን÷
1∙ ኢየሱስ ክርስቶስ  የዓለም መድኃኒት መሆኑን÷ ቀደም ሲል እንዳነሳነው ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም የመጣበት ዋነኛ ዓላማ በኃጢአት የወደቀውን የሰው ልጅ በጽድቅ ለማንሳት፣ የስጋንና የነፍስንም ደዌ ሊፈውስ ነው። ፈዋሽ መሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ተገልጿል። “መዳንም በሌላ በማንም የለም እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና” የሐዋ 4:12። ይህ የሚያስረዳን ኢየሱስ ክርስቶስ ለማንኛው በሽታና ደዌ ፍቱን መድኃኒት መሆኑን ነው። የሰማርያ ሰዎችም “… እርሱም በእውነት ክርስቶስ የዓለም መድኃኒት እንደሆነ እናውቃለን …” በማለት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
2 ∙ለመንፈሳዊ ዕውርነት መፍትሄው ክርስቶስ እንደሆነ÷ ኢየሱስ ክርስቶስ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ”(ዮሐ 8:12) ብሏል። ያኔ አዳምና ሔዋንን በገነት ውስጥ ያሳወረ ሰይጣን ዛሬም ቢሆን ብዙዎችን ለማሳወር እንደተራበ አንበሳ አያገሳ ይዞራል  ። ለዘህ ደግሞ ትልቁ መፍትሄ መንፈሳዊ ጨለማን ወደ ሚያርቀው ወደ ክርስቶስ መጠጋት ነው። ወደ እርሱ መጠጋት ማለት በእርሱ መኖርና ከመንፈሳዊ ዕውርነት  መላቀቅ ማለት ነው።
3∙ ላዳነንና ብርሃን ለሰጠን አምላካችን መስካሪዎች መሆን እንዳለብን÷ በጨለማ ዓለም ውስጥ ስለ ብርሃን መመስከር ዋጋ የሚያስከፍል ነገር ቢሆንም ልባችንን ከጨለማና ከዕውርነት ስላወጣው ብርሃናችን የመመስከር መንፈሳዊ ግዴታ አለብን። ብርሃናችን እርሱ ክርስቶስ ነው። በአምላካችን ቸርነትና ምህረት ደኅንነትንና ብርሃንን ካገኘን ለሌሎችም በኃጢአት ሕይወት ውስጥ ላሉት ስለ ብርሃናችን ክርስቶስ እየነገርናቸው ከጨለማ እንዲወጡ ማድረግ አለብን። ውድ አንባብያን ሆይ በመልካም መንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ ዘመናችንን እንድናሳልፍ እግዚአብሔር ይርዳን አሜን ።
                       
                                           ወስብሐት ለእግዚአብሔር 

 
“ከጠላቶቻችንም እጅ እንዲአድነን የእግዚብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ከሴሎ እናምጣ አሉ፡፡”

                                                                                                          በመ/ር ሣህሉ አድማሱ

ታቦት
ታቦት የሚለው ቃል ቤተ አደረ ከሚለው ግሥ የወጣ ነው፡፡ ነቢዩ ሙሴ ታቦትን ከግራር እንጨት እንዲሠራ ከእግዚአብሔር ታዘዘ (ዘፀ.25፥1)
የመጀመሪያው የታቦት አሠራር አራት ማዕዘን ያለው ሣጥን የሚመስል ሲሆን ርዝመቱ 125 ወርዱ 75 ቁመቱ 75 ሳንቲ ሜትር ያህል ነው፡፡
ታቦቱ በወርቅ የተለበጠ፣ መክደኛውም ከወርቅ የተሠራ ነበር፡፡ በላዩም የሁለት ኪሩቤል ስዕል ተቀርጿል፡፡  የታቦቱም አገልግሎት አሥርቱ ቃላት የተጻፉባቸው የሁለቱ ፅላት መኖሪያ ነው፡፡
እግዚአብሔር በታቦቱ አማካኝነት ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ይገናኝ ነበር፡፡ (ዘፀ.25፥3) ነቢዩ ሙሴ ታቦቱን አሠርቶ ከመገናኛው ድንኳን አኖረው፡፡ የእስራኤልም ሕዝብ ታቦቱን እየያዙ ይጓዙ ነበር፡፡ ዮርዳኖስን ሲሻገሩና የኢያሪኮን ቅፅር ሲዞሩ ካህናቱ ታቦቱን ተሸክመው ከፊት ከፊት ይሄዱ ነበር፡፡ (ኢያ.3፥6)
የእግዚአብሔር ታቦት በኤሊ ዘመን!!
በኤሊ ዘመን ሁለቱ የኤሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ ከእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት ጋር ነበሩ፡፡ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ሰፈር በገባ ጊዜ እስራኤል ሁሉ  ታላቅ እልልታ አድርገዋል፡፡
ይሁን እንጂ ፍልስጥኤማውያን የእልልታውን ድምፅ በመስማታቸው ከእስራኤላውያን ጋር ተዋጉ፡፡ ከእስራኤል ሰላሳ ሺህ እግረኞች ወደቁ፡፡ የእግዚአብሔርም ታቦት በፍልስጥኤማውያን ተማረከች፡፡ ሁለቱም የኤሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ በእግዚአብሔር ቁጣ ተቀሰፉ፡፡
ካህኑ ኤሊ ያን ጊዜ የዘጠና ስምንት ዓመት ሽማግሌ ነበር፡፡ ዐይኖቹም ማየት እስኪሳናቸው ድረስ ፈዝዘው ነበር፡፡ የታቦተ እግዚአብሔርን መማረክ እና የልጆቹን የአፍኒንና የፊንሐስን መሞት ሲሰማ ከተቀመጠበት ወንበር ወድቆ ሞተ፡፡ ምራቱ የፊንሐስ ሚስት አርግዛ ልትወልድ ተቃርባ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር ታቦት እንደተማረከች፣ ባልዋና አማትዋ እንደሞቱ በሰማች ጊዜ ባልዋና አማትዋ ስለሞቱ ክብር ከእስራኤል ለቀቀ ስትል የልጇን ስም ኢካቦድ ብላ ጠራችው፡፡
ፍልስጥኤማውያን የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ከአቤኔዘር  ወደ አዛጦን ይዘውት ሄዱ፡፡ በዚያም ወደ ዳጎን (ጣኦት/ቤት አስገቡት፤ በዳጎንም አጠገብ አኖሩት፡፡
ይሁን እንጂ በማግስቱ ዳጎን /ጣኦቱ/ በእግዚአብሔር ታቦት ፊት በግምባሩ ወድቆ ነበር፡፡ እንደገና ቢአነሱትም በድጋሚ በግምባሩ ወደቀ፡፡ እጆቹም፣ እግሮቹም ተሰባበሩ፡፡ የእግዚአብሔርም እጅ በአዛጦን ሰዎች ላይ ከበደች፡፡ በእባጭም መታቸው፡፡ በዚያን ጊዜ የአዛጦን ሰዎች የእስራኤል አምላክ የእግዚአብሔር ታቦት በእኛ ዘንድ አይቀመጥ አሉ፡፡ የእግዚአብሔር ታቦት ከአዛጦን ወደ ጌት ተመለሰች፡፡
የጌትም ሰዎች በእባጭተ መቱ፡፡ ከዚያም የእግዚአብሔር ታቦት ወደ አስቀሎና ተመለሰች፡፡ የአስቀሎናም ሰዎች በእባጭ ተመቱ፡፡ የከታመይቱም ዋይታ እስከ ሰማይ ደረሰ፡፡
በዚሁ ሁናቴ የእግዚብሔር ታቦት በፍልስጥኤማውያን ከተሞች ለሰባት ወራት ያህል ተቀመጠች፡፡
የእግዚአብሔር ታቦት ከፍልስጥኤም ወደ ቤትሳሚስ!!
ፍልስጥኤማውያን ለእስራኤል አምላክ ታቦት ክብርን ለመስጠት ስለበደል መስዋዕት የወርቅ ዕባጮች በማቅረብ የወርቁን ዕቃ በሣጥን ውስጥ አድርገው የእግዚአብሔርን ታቦት በሰረገላ ጭነው ከፍልስጥኤማውያን ድንበር ላይ ወደ ሚገኘው ወደ ቤትሳሚስ በሚወስደው መንገድ በማቅናት በኮረብታው ላይ ወዳለው ወደ አሚናዳብ ቤት አስገብተው አስቀመጡት፡፡
የእግዚአብሔር ታቦት በአሚናዳብ ቤት!!
የእግዚብሔር ታቦት በአሚናዳብ ቤት  መቀመጥ  ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ታቦቱን እንዲጠብቅ እስራኤላውያን የአሚናዳብን ልጅ አልአዛርን ቀደሱት፡፡ የእግዚአብሔርም ታቦት በአሚናዳብ ቤት ለሃያ ዓመታት ያህል ተቀመጠች፡፡
የእግዚአብሔር ታቦት ከአሚናዳብ ቤት ወደ ኢየሩሳሌም!!
ነቢዩ ዳዊት የእግዚአብሔርን ታቦት ከአሚናዳብ ቤት ወደ ኢየሩሳሌም አመጣ፡፡ ነቢዩ ዳዊት የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም ሲያመጣ ኦዛ የተባለ ሰው በድፍረት ታቦቱን በእጁ በመንካቱ ተቀሰፈ፡፡ (2ሳሙ.6) ጠቢቡ ሰሎሞንም አባቱ ዳዊት ከአሚናዳብ ቤት ያመጣውን የእግዚአብሔር የቃልኪዳን ታቦት ራሱ ባሠራው ቤተ መቅደስ አስቀመጠ፡፡ (1ነገ.8)
የእግዚአብሔር ታቦት ከኢየሩሳሌም ወደ ኢትዮጵያ!!
በብሉይ ኪዳን ንግሥተ ሳባ፣ በሐዲስ ኪዳን ንግሥተ አዜብ፣ በክብረ ነገሥት ንግሥት ማክዳ በመባል የምትታወቀው ኢትዮጵያዊት ንግሥት የንጉሥ ሰሎሞንን ዝና በሰማች ጊዜ በግመሎች ላይ ሺቱ፣ ወርቅና እንቁ አስጭና ወደ ኢየሩሳሌም ሂዳ ለንጉሡ ለሰሎሞን ሰጠችው፡፡ ንጉሥ ሰሎሞንም በገዛ እጁ ከሰጣት ሌላ የወደደችውን ሁሉ ስጦታ ለሳባ ንግሥት ሰጣት፤ እርስዋም ከባሪያዎችዋ ጋር ወደ ምድርዋ ተመለሰች (1ነገ.10፥1-13)
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ አስተምህሮ መሠረት ንግሥተ ሳባ ከንጉሥ ሰሎሞን ቀዳማዊ ምኒልክን ወለደች፤ ቀዳማዊ ምኒልክም ካደገ በኋላ ወደ እናቱ ወደ ንግሥተ ሳባ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ ሦስት መቶ አስራ ስምንት ሌዋውያን እና ካህናትን ይዞ ሲመጣ ታቦተ እግዚአብሔርን (ታቦተ ፅዮንን) ይዞ መጣ፡፡
የእግዚአብሔር ታቦት በአክሱም ፅዮን!!
አክሱም
የአክሱም ከተማ የንግሥተ ሰባ መናገሻ ከተማ ሆና አገልግላለች፤ አክሱም ጥንታዊት፣ ቀዳማዊት፣ የነገደ ኩሽ መዲና፣ በኋላም የሰባውያን መዲና መሆንዋ ተረጋግጧል፤ አክሱም የኢትዮጵያ መናገሻ ከተማ ሆና ከአንድ ሺህ ዓመት በላይ እንደኖረች የታሪክ መዛግብት ይስማማሉ፤ የተመሠረተችውም እንደ ሰንሰለት በተያያዘ ኮረብታ መካከል ነው፤ ከሰሜናዊ ምሥራቅ አንስቶ እስከ ሰሜናዊ ምዕራብ በሚዘልቅ ኮረብታ ተከባለች፤ የአክሱም ከተማ ከክርስቶስ ልደት በፊት ከሁለት ሺህ ዓመተ ዓለም አስቀድሞ እንደተመሠረተች የተለያዩ የታሪክ መዛግብት ይናገራሉ፡፡
የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት ከንጉሥ ሰሎሞን እና ከንግሥተ ሳባ አብራክ የተከፈለው /የተወለደው/ ቀዳማዊ ምንይልክ እና አብረውት ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ ሌዋውያን ጋር የንግሥተ ሳባ መናገሻ በሆነው በአክሱም ፅዮን በቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን  አስቀምጠዋል፡፡ በዓሉም በየዓመቱ ህዳር 21 ቀን ዓለም አቀፍ በዓል ሆኖ በከፍተኛ ድምቀት ሲከበር ቆይቷል፤ አሁንም በታላቅ ድምቀት እየተከበረ ይገኛል፡፡

 
የየካ አባዶ ምሥራቀ ፀሐይ ቅዱስ ሚካኤል እና 24 ካህናተ ሰማይ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ቤት ተከበረ!!

                                                                                                                                               በመ/ር ሣህሉ አድማሱ

5954

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በየካ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት  ሥር የሚገኘው እና ለአስራ አራት ተከታታይ ዓመታት ያህል ሲገነባ የቆየው የየካ አባዶ ምሥራቀ ፀሐይ ቅዱስ ሚካኤል እና አርባእቱ እንስሳ ብፁዕወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፣
ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራአስኪያጅ መምህር ጎይቶም ያይኑ፣ የየካ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት የሥራ ኃላፊዎች፣ የገዳማትና አድባራት አስተዳደሪዎች፣ የደብሩ ካህናትና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች እና በርካታ ምዕመናን በተገኙበት እሁድ ህዳር 10 ቀን 2010 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ተባርኮ የቅዳሴ ቤቱ በዓል በታላቅ ድምቀት ተከብሯል፡፡
ይህ ታሪካዊና ዘመናዊ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ተባርኮ የቅዳሴ ቤቱ  በዓል በተከበረበት ወቅት የህንጻውን ግንባታ ሥራ በማፋጠን ትልቁን የማስተባበር ድርሻ ሲያከናውኑ የቆዩ መሆናቸው የሚነገርላቸው የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ፀሐይ አባ ሀብቴ ባቀረቡት ሪፖርት እንደተገለፀው የየካ አባዶ ምሥራቀ ፀሐይ ቅዱስ ሚካኤል እና 24 ካህናተ ሰማይ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በ390 ካሬ ሜትር ስፋት ላይ ያረፈ ባህል ተኮር እና ታሪካዊ ሕንጻ ነው፡፡
ከዋናው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ጋር የ25 ሜትር ርቀት ባለው ድልድይ የተያያዘ ሕንጻ ቤተልሔም ተሠርቶ የግንባታ ሥራው የተጠናቀቀ ስለሆነ ከሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ጋር ተባርኮ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡
ለሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ አጠቃላይ ግንባታ ሥራ ከ8 ሚሊዮን 4 መቶ ሺህ ብር ያላነሰ ገንዘብ ወጪ ሆኗል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ ከ63 ሺህ ካሬ ሜትር ስፋት በላይ የይዞታ ቦታ ቢኖረውም በአንድ አንድ ግለሰቦች የይዞታ ይገባኛል ጥያቄ እየተነሳ አለመግባባት ሲከሰት ቆይቷል፡፡
ይሁን እንጂ በደብሩ ቀጣይ የሥራ ዕቅድ መሠረት ችግሮቹ ሙሉ በሙሉ ተወግደው የአረጋውያን መርጃ ማዕከል፣ የአብነት ትምህርት ቤት እና የልማት ተቋማት ሥራዎች እንደሚከናወኑ የደብሩ አስተዳዳሪ በሪፖርታቸው አብራርተዋል፡፡
በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የቅዳሴ ቤቱን በዓል ለማክበር ለተሰበሰበው በርካታ ምዕመናን ባስተላለፉት አባታዊ መልእክት ይህንን ታላቅ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በገንዘብ፣ በሐሳብና በጉልበት ተባብራችሁ ለፍጻሜ ያደረሳችሁ ሁላችሁም እንኳን ደስ አላችሁ!!
በኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ቀኖና መሠረት ይህንን ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በጸሎትና በቅዱስ ቅብአት ባርከነዋል፤ ቀድሰነዋል፡፡ ከልዩ ልዩ ሕንጻዎች ተለይቶ የእግዚአብሔር ቤት ሆኗል፡፡ ከዛሬ ጀምሮ ልጆቻችሁ ይጠመቁበታል፤ ቅዱስ ሥጋው ይፈተትበታል፤ ክቡር ደሙ ይቀዳበታል፣ ቦታው ህፃናት የሚማሩበት፣ አረጋውያን የሚጦሩበት ማዕከል እንዲሆን እንመኛለን በማለት ቅዱስነታቸው አባታዊ ትምህርት ሰጥተው እና ቃለ ምዕዳን አስተላልፈው የበዓሉ መርሐ ግብር በጸሎት ተጠናቋል፡፡

 
ዝርዝር ፅሁፍ...
<< ጀምር < ወደኋላ 1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 ወደፊት > መጨረሻ >>

ገጽ 1 ከ 64

አድራሻ

አዲስ አበባ ፤ ኢትዮጵያ

ኢ-ሜይል: aadioces@gmail.com

ድረ ገጹ ውስጥ ይፈልጉ

ሀሳበ ባሕር(የዘመን ቁጥር)

ባሕረ ሐሳብ የዘመን መቁጠሪያ

ግጻዌ