ቁጥራቸው ከ3,000 በላይ የሚገመት በደቡብ ኦሞ የዳንሰነች ማኅበረሰብ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነትን በመቀበላቸው ጥምቀተ ክርስትና ተፈጸመላቸው

0669

መሠረቷ ብሉይ ኪዳን፣ ጉልላቷ ሐዲስ ኪዳን የሆነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕገ ኦሪትን በዘጠኝ መቶ ዓመተ ዓለም በቀዳማዊ ምኒሊክ አማካኝነት ተቀብላ አምልኮተ እግዚአብሔርን ስታስፋፋ ከቆየች በኋላ አዲስ ኪዳንን ደግሞ በ34 ዓመተ ምሕረት በጃንደረባው /ባኮስ/ አማካኝነት የተቀበለች ሲሆን ሥርዓተ ክህነትን በዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን /ፍሬምናጦስ/ በኩል ተቀብላ ክርስትናን ስታስፋፋ ቆይታለች፡፡
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል “አዝመራው ብዙ ነው ሠራተኞቹ ግን ጥቂቶች ናቸው የመከሩ ባለቤት ሠራተኛ እንዲጨምር ለምኑት” በማለት እንዳስተማረው ከሕገ እግዚአብሔር ርቀው፣ በተለይም እግዚአብሔርን በማምለክ ፈንታ ለድንጋዩና ለዛፉ እየተንበረከኩ እና እየሰገዱ የሚኖሩ የአዳም ዘሮች በርካታ ስለሆኑ ቤተ ክርስቲያን ወደ እነርሱ ሂዳ ወንጌልን መስበክ እንደሚገባት ይታመናል፡፡
እነዚህ ወንጌል ያልደረሳቸው የአዳም ዘሮች ከአፍሪካዊነታቸው ጋር የማይስማማ ብዙ የባህል ውጥንቅጥ ስላለባቸው ከዚያ ሁሉ ለመላቀቅ እንዲችሉ ቤተ ክርስቲያን የበኩልዋን ድርሻ መወጣት እንደሚገባት የታወቀና የተረዳነው፡፡
 ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ በተሰኘው መጽሐፋቸው ገፅ 3 ላይ እንዳሰፈሩት “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያበረከተቻቸው ስጦታዎች ብዙ ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል ሙሉ ትምህርት፣ ፍጹም ቋንቋ ከነፊደሎች፣ ሥነ ጽሁፍ ከነጠባዩ፣ ኪነ ጥበብ በየዓይነቱ፣ ሥነ ጥበብ በየመልኩ፣ ታሪካዊና ጥንታዊ ቅርስ፣ እምነት ከነፍልስፍናው፣ ነፃነት ከነክብሩ፣ አንድነት ከነጀግንነቱ፣ አገር ከነድንበሩ፣ ስም ከነትርጉሙ” ብለው ጽፈዋል፡፡ አሁንም ቢሆን ትውልዱ ለሃይማኖት ተቆርቋሪነትን ይዞ እንዲያድግ በማስተማርና በማበረታታት ቤተ ክርስቲያን የበኩሏን ድርሻ እየተወጣች ትገኛለች፡፡
ከእነዚህም መካከል የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በርዕሰ መዲናው የሚገኙትን የተለያዩ የብሔረሰቦች ሕዝቦችን በመንፈሳዊ አመራርና በስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ የላቀ አገልግሎት ሲያበረክት የቆየ ሲሆን ከዚህም ጎን የኢኮኖሚ እጥረት ባለባቸው ሌሎች አሕጉረ ስብከት ዘርፈ ብዙ የበጀት ድጋፍ ሲያደርግ የቆየ እና አሁንም በማድረግ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ በተለይም ደቡብ ኦሞ እየተባለ በሚጠራው ዞን ሥር የሚገኙ አሥራ ስድስት ማኅበረሰብ ማለትም፡-
1.ሐመር             9. ፀማይ 
2.በነ                 10. ቦዴ
3.ኞንጋቶም         11. ካሮ
4.ዳንሰነች           12. ሱርማ
5.ሙርሲ             13. ባጫ
6.ኦሪ                 14. ዲሜ
7.ሚሊ               15. ሚርሌ
8.ኤሪቦሌ            16. ብራይሌ /ወይጦ/

0332

በሚገኙበት በረሃማና ደጋማ ቦታዎች የአብያተ ክርስቲያናት ግንባታ እና የአዳዲስ አማኞች ወደ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖት መምጣትና መጠመቅ ትልቁን ድርሻ ይዞ እየተጓዘ ያለው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት መሆኑ በማንም ዘንድ አይዘነጋም፡፡
ለእነዚህ አምላክ የለሽ ሕዝቦች ወደ ክርስትና መምጣትና ከ38 ያላነሱ አብያተ ክርስቲያናት ግንባታ በዋነኛነት የማስተባበሩን አገልግሎት እያፋጠነ የሚገኘው የደቡብ ኦሞ የአብያተ ክርስቲያናት አሳፋሪ ኮሚቴ ሲሆን ሀገረ ስብከቱ የጽ/ቤቱ መገልገያዎች ከሆኑት ቢሮዎች መካከል አንድ ዘመናዊ ቢሮ በነፃ በመፍቀድ፣ በአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት እየተዘዋወረ የገንዘብ፣ የማቴሪያልና የቁሳቁስ እርዳታ እንዲጠይቅ የትብብር ደብዳቤ በመጻፍ፣ ኮሚቴው የተለያዩ ኢግዚቢሽኖችን እንዲአዘጋጅ መንግሥታዊ ለሆኑ እና መንግሥታዊ ላልሆኑ ተቋማት ጭምር የትብብር ደብዳቤ በመጻፍ እንደዚሁም ተጠማቂ ማህበረሰቦቹ ባሉበት ድረስ አገልጋዮችን በመላክ ሀገረ ስብከቱ መጠነ ሰፊ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡
በዚሁ መሠረት በዘንድሮው 2009 ዓ.ም ለዘጠኝ ተከታታይ ቀናት በተደረገው መንፈሳዊ ጉዞ በነምረሙዝ ኪዳነ ምህረትና በኦሞ ራቴ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ቁጥራቸው ከ3000 በላይ የሚገመት የዳንሰነች ማህበረሰብ የኢትዮጵያ  ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖትን  አምነው በመቀበላቸው ሥርዓተ ጥምቀት ተፈጽሟላቸዋል፡፡

 

አድራሻ

አዲስ አበባ ፤ ኢትዮጵያ

ኢ-ሜይል: aadioces@gmail.com

ድረ ገጹ ውስጥ ይፈልጉ

ሀሳበ ባሕር(የዘመን ቁጥር)

ባሕረ ሐሳብ የዘመን መቁጠሪያ

ግጻዌ