መንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም

የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ገነተ ጽጌ ቅ/ጊዮርጊስ

የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለም

የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

መንበረ ጸባዖት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል

የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ርዕሰ አድባራት መንበረ ፀሐይ እንጦጦ ማርያም

የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ምስካየ ኅዙናን መድኃኔኃለም ገዳም

የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም

የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ደብረ ጽጌ ቅድስ ኡራኤል

የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

መንበረ መንግሥት ቅ/ገብርኤል ገዳም

የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ደብረ ኃይል ራጉኤል

የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

http://www.addisababa.eotc-churches.org/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/590538kidste_mariam.jpg http://www.addisababa.eotc-churches.org/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/895720giorgis.jpg http://www.addisababa.eotc-churches.org/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/903816bole_medhaniealem.jpg http://www.addisababa.eotc-churches.org/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/683566trinity.jpg http://www.addisababa.eotc-churches.org/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/821897entoto_mariam.jpg http://www.addisababa.eotc-churches.org/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/310283meskaye_1.jpg http://www.addisababa.eotc-churches.org/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/904160BEATA_MARIAM.jpg http://www.addisababa.eotc-churches.org/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/578084urael.jpg http://www.addisababa.eotc-churches.org/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/812647gebrie_gedam.jpg http://www.addisababa.eotc-churches.org/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/681179raguel.jpg
ሙስናና ብልሹ አሠራር እንዲቆም ብፁእ ወቅዱስ ፓትርያርኩ አሳሰቡ

ብ ፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ሚያዝያ 5 ቀን 2005 ዓ.ም በአዲስ አበባ ደቡብ ሀገረ ስብከት በደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው የቅዱስ ያሬድ 1500 የልደት በዓል ባከበሩበት ወቅት ባስተላለፉት አባታዊ መልእክት፡፡

‹‹ለዛሬው በዓል ያደ ረሰን አምላካችን እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን›› የታላቁን ሊቅ የቅዱስ ያሬድን በዓል ስናከብር እግዚአብሔር በረድኤት ይጠብቀናል፡፡ ታላቁ የዜማ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ የደረ ሰውን የዜማ ድርስት ከአእዋፍና ከመላእክት የተማረ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ቅዱስ ያሬድ ባስተላለፈው የዜማ ትምህርት ዛሬ እልፍ አእላፋትን ሊቃውንት እናያለን፡፡ ለቅዱስ ያሬድ የተሰጠው ፀጋ እጥፍና ድርብ ነው፡፡ በደረሰው የዕዝል፣ የአራራይና የግእዝ የዜማ ድርስት ለአሁኑ ትውልድ ትልቅ ሰማያዊ ሀብት አስተላልፏል፡፡ ይህ አንድ ሺ አምስት መቶ ያስቆጠረው ትም ህርት በአሁኑ ጊዜ የበለጠ ተወዳጅ ሆኖ ይታያል ትውልዱ በዜማው ልቡ እየተመሰጠ ነው ያለው፡፡

የሰማይ ሥርዓት በምድር ተሠርቷልና፡፡ ይህ የሰማይ ሥርዓት የመላ እክት ምስጋና ነው፡፡ እግዚአብሔር በደቂቀ አዳም መመስገን ፈልጎ ነው ይህን የመላእክት ሥርአት ወደ ሰው ያስተላለፈው በዚህ ሰማያዊ ሥርአት የቤተ ክርስቲያን ክብር ተጠብቆ ይኖራል፡፡ ይህም ለምድረ ኢትዮጵያ ብቻ የተሰጠ ሀብት ነው፡፡ በዚህ ሥርአት ቤተ ክርስቲያን ደምቃ እና አሸብርቃ ትታያለች፡፡ በሌ ላው ዓለም የቅዱስ ያሬድ ዜማ ስለሌለ ዜማቸው እኛን አያስደስትም ምን አልባት እነሱን ያስደስት ይሆናል፡፡ የፈረንጆቹ ዜማ ቅጥ የሌለው ዜማ ነው፡፡ የያሬድ ዜማ ለዜማው ብቻ ሳይሆን ሙዚቃውም ከዚህ ዜማ ውጭ አይደለም፡፡ ዛሬ እልፍ አእላፋት ውሉደ ያሬድ አሉ፡፡ አሁን ከፊታችን ያለችሁት ሊቃውንት መከራ አይታችሁ ውሻ ጮሆባችሁ ውሻ ነክሷችሁ የተማረችሁ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ወደፊትም እንደ ዘመኑ ስልጣኔ ዜማው እየተሻሻለ ይመጣል፡፡ ይህ የቅዱስ ያሬድ የዜማ ትምህርት በአዳሪ ትምህርት ቤት እንዲሰጥ እንመኛለን፡፡ አሁንም ቢሆን ከወትሮው የተሻለ ፍንጭ እየታየ ነው ያለው፡፡ ቤተክርሰቲያን ለዚህ ሥርዓት መሻሻል ብርቱ ጥረት ታደርጋለች፡፡ ቤተ ክርስቲያን ቤተ ርህራሄ ናት፡፡ እግዚአብሔር አምላክ እኔ ቅዱስ ነኝ እና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ እንዳለው ቤተ ክርስቲያን ቅድስት መሆን አለባት፡፡

አሁን እንደምናየው ግን መልኳን እየለወጠች ነው፡፡ ነገሮች ሁሉ መልካቸውን እየለወጡ ናቸው፡፡ ቅድስናችን እየተሸራረፈ ነው፡፡ ዛሬ በቤተ ክርስቲያን አካባቢ ጥሩ ያልኑ ነገሮች ይሰ ማሉ፡፡ አደራችሁን እንጠንቀቅ፡፡ ዓላማ ችንንም አንልቀቅ ዓለም እንደሆነች አስቸ ጋሪ ናት፡፡ ብዙ የሚያብረቅርቅ ነገር አለ፡፡ ተገቢ ያልሆነ የሀብት ክምችት አለ ከቤተ ክርስቲያን ጋር ያልተያያዘ ድርጊት ይታያል፡፡ ቤተክርስቲያን የሀቅ፣ የጽድቅ እና የእምነት ቦታ ናት፡፡ አሁን ግን ይህ ቅዱስ ሀብት እየተጓደለ ነው ያለው ማህበረ ምዕመናን ግን ያላቸውን እና የሌላቸውን እየሰጡ ናቸው፡፡ ገንዘባችሁን በእውነተኛው ቦታ ማዋል አለባችሁ፡፡ እምነቱ፣ ሀቀኝቱ፣ መል ካም አስተዳደሩ ከቤተ ክርስቲያን መገኘት አለበት ፡፡ ለትውልዱ መልካም ምሳሌ መሆን አለባት፡፡ ቤተ ክርስቲያን መሸራረፍ የለባትም በመሠረቱ ሰው በባህርዩ ደካማ ነው፡፡ ድካምም ይሰማዋል እግዚአብሔር አምላክ ሁላችሁንም ይባርካችሁ ከታላቁ ሊቅ ከቅዱስ ያሬድ በረከት ያሳትፋችሁ ዘመኑን የሰላም ዘመን ያድርግልን፡፡ ፆሙ ለሀገር የሚጠቅም የሀገርን አንድነት የሚአስጠብቅ ያደርግልን ለብርሃነ ትንሳ ኤው በሰላም ያድርሰን በማለት ሰፋ ያለ አባታዊ ትምህርትና ቃል ምዕዳን አድር ገዋል፡፡

በመጨረሻም የዝግጅት ክፍላችን በቅዱስነታቸው አባታዊ መልእክት በመመራት ከላይ እስከ ታች ከታች እስከ ላይ ያለው የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ሁሉ ከሙስና እና ከብልሹ አሠራር በመላቀቅ፡፡ መል ካም አስተዳደር እንዲሰፍን፣ ልማት እንዲ ስፋፋ ጥረት ማድረግ ይገባል እንላለን፡

ምንጭ ኆኅተ ጥበብ መጽሔት

 
በሃይማኖት ሽፋን “ተረፈ አይሁዳዊነት በኤልያሳዊነት ስም ሲበቅል”

ሰሞኑን በከተማችን አዲስ አበባ ““የኢትዮጵያ ትንሳኤ ሊያረጋግጥ ኃያል ባለስልጣን ቅዱስ ኤልያስ ከብሔረ ሕያዋን መጥቷል፤ የአለም ፍጻሜ ቀርቧል” የሚሉ አካላት ተነስተዋል፡፡ እነሱ እንደሚሉት ነብዩ ኤልያስ መጥቶ አዲስ አበባ ይገኛል፡፡ ቤተመንግሥቱንና ቤተክህነቱን ለማጥራት ተዘጋጅቷል ፡፡

ከሚያጠራቸው የቤተክህነት ጉዳዮችም ሦስቱ ትኩረት አግኝተዋል ይላሉ፡፡ “የመጀመሪያው ኦርቶዶክስ የሚለው ስም ስህተት ነው ፤ ስማችን ተዋህዶ ነው ፤ መለበስ ያለበት ልብስ ነጭ ብቻ ነው ፤ እሱም ቢሆን ጥለቱ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ መሆን መቻል አለበት ፤ አሁን ያሰርነውን ክር በመበጠስ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ክር ማሰር አለብን” የሚል ነው፡፡

በየአጋጣሚው ቤተክህነቱንና ቤተ መንግሥትን በመንቀፍ አሁን የሚታዩትን ችግሮች መሰረት አድርጎ ህዝቡ መጥቷል የተባለው ኤልያስን መከተል እንጂ ወደ ቤተክርስቲያን መሄዱ ጥቅም እንደሌለው እየተነገረ ነው፡፡

ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ውስጥ አንዲት ሴት ”መሲህን ልወልድ ነው” እያለች ሰዎችን ታስከትል ነበር፡፡ ይህቺ ሴት አስገራሚ በሆነ ሁኔታ በየገዳማቱ እየዞረች ካህናቱን ሁሉ ለማንበርከክ ተንቀሳቅሳለች፡፡ ለዚህም ወንጪ ቂርቆስ ላይ ያደረገችውን ማስታወስ በቂ ነው፡፡

የዚህች ሴት አካሔድ አነጋጋሪ የሚሆነው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ በደሙ በመሠረታት፣ ሥጋውና ደሙም በሚፈተትበት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የአይሁድ ወገኖች አስተምህሮ የሚመስል ሰበካ ይዛ መገኘቷ ነው፡፡ የክርስቶስ ዳግም ምጽአት በምትጠባበቅ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ክርስቶስ ገና እንደሚወለድ ያለ አስተምህሮ ሲነገር መስማት ማሳፈሩ ብቻ ሳይሆን በጊዜው ቤተ ክርስቲያን ትንሹም ትልቁም በወደደ ጊዜ የሚሻውን የሚፈጽምባት፣ የሚናገርባት ተቋም አይደለችም፡፡

ሴቲቱ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሊታሰብ የማይችል በማሰቧ፣ ሊነገር የማይችል በመናገሯ በአብዛኛው የክርስቲያን ወገን ይታሰብ የነበረው የአንዲት ሴት ከንቱ ቅዠት ተደርጎ ነው፡፡ ከዚህ አልፎ ተመሳሳይ ዝንባሌዎች ያቆጠቁጣሉ ብሎ ያሰበ የለም፡፡

እነሆ ዛሬ ደግሞ ሌላ የአይሁዳዊነት ዝንባሌ ያለው አስተምህሮ በኤልያስ ስም በተደራጀ ቡድን አማካኝነት ማብቀል ጀምሮ እስከ አራት መቶ ተከታዮች እንዳሉት እየተነገረ ነው፡፡ አስገራሚው ይኸው አስተምህሮ ተለጥፎ የመጣው በዚህችው በመከራ ውስጥ በምትጓዝ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መሆኑ ነው፡፡ ስሙንም በተዋሕዶነት ሰይሞ ሲጓዝ አላፈረም፡፡ መከፋፈል፣ ማሰለፍ የሚፈልገውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንን ነው፡፡ አስተምህሮው የተደበላለቀና ወጥ ያልሆነ ዘርፍ፣ መልክ፣ መነሻም መድረሻም የሌለው ክርስትና ይሁን አይሁዳዊነት ፖለቲካ ይሁን ሃይማኖት ጥንቆላ ይሁን እብደት ያለየለት እንቅስቃሴ ነው፡፡

ይህ ቡድን አውቆም ሆነ ሳያውቅ ጥለን ወደመጣነው እርሾ ወደ አይሁዳዊነት ያዘነበለ አስተምህሮ ይዞ መገኘቱ ብቻ ሳይሆን ቤተ ክርስቲያንን ለመከፋፈል አንዱን አንሥቶ ሌላውን ለመጣል የሚሞክር አፍራሽ አካሔድም የያዘ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ላይ ባለፉት ዘመናት ከተወረወሩት ፍላጻዎች ተከትሎ የመጣ በአቅሙ ፍላጻ ሆኖ ለማደግ የሚተጋ ነው፡፡

በዚህች ቤተ ክርስቲያን ባለፉት ዘመናት በብሕትውና ስም በአጥማቂነት ስም ብዙዎች የተለያዩ ፍላጎቶቻቸውን ለማስተጋባት ምእመናንን ግራ በማጋባት ተሰልፈው እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ሁሉም እየታዩ መጥፋታቸው እንዳለ ሆኖ ያጠፉት፣ ተስፋ ያስቆረጡት ያሰናከሉት መንጋ እንዳለም አይረሳም፡፡ በአብዛኛው ግን አሁን አሁን እንደሚታዩት መሠረት የለሽ ከክርስትና ሃይማኖት እሳቤ ፍጹም የወጣ ጽንፍ ይዘው ግን ታይተዋል ማለት አይቻልም፡፡ አብዛኛውም ምእመናን እርካታ ሊሰጣቸው ያልቻለውን የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳደር በመንቀፍ ስለሚመሠረቱ ተከታዮችን በቀላሉ ለማግኘት አስችሏቸው ነበር፡፡ በአብዛኛው የባሕታውያኑና የአጥማቂዎቹ ትኩረት አስተዳደሩን፣ አገልጋይ ማኅበራትን፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶችን፣ ግለሰቦችን መንቀፍ ላይ የሚያተኩርና ከዚያ አለፍ ሲል የራሳቸውን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ለመደንገግ ሲጥሩ መታየታቸው ነው፡፡

እነዚህ የአሁኖቹ የአይሁዳዊነት ዝንባሌ ያላቸው እንቅስቃሴዎች ግን የተናቁ ቢመስሉም የአካሔድ ሚዛኑ ፍጹም ፀረ ክርስትና ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሚሠሩ እንደሆነ ይናገሩ እንጂ የሚያሳስባቸው የስብከተ ወንጌል ሥርጭት አይደለም፡፡ የቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት አቅም ስለማደግ አለማደጉ አይደለም፡፡ አስተዳደራዊ መሻሻል ስለማምጣት አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ውስጥ ለውስጥ ለማዳከምና ለመከ ፋፈል ስለሚሠራው የተሐድሶ ቡድን አይደለም፡፡ ወይም በሀገሪቱ እየተስፋፋ ስላለው ዓለማዊነት አይደለም፡፡ በሀገሪቱ እየተስፋፋ እንደሆነ ስለሚነገርለት ግብረሰዶምና እጅግ የከፋ የኃጢአት ሥራ አይደለም፡፡ ስለ ሰላም ስለ ዕርቅ አይደለም፡፡ እነዚህ ወገኖች የሚያሳስቧቸው ነገሮች ሲመረመሩ የጸሐፍት ፈሪሳውያን እርሾ ከቤተ ክርስቲያን የመወገዱ ጉዳይ ያንገበገባቸውና የቤተ ክርስቲያን አገልግሎትን ሊያሳድጉ ሊያሰፉ ሊያጠናክሩ የሚችሉ ፍንጮች መታየታቸው ያበሳጫቸው መሆኑን መረዳት እንችላለን፡፡ እነዚህ ወገኖች ነግቶ በመሸ ቁጥር የሚናገሯችው የተደበላለቁ ያልሰከኑ ገና እየተደራጁ ያሉ ዝብርቅርቅ ሐሳቦች ያሏቸው ስለሆኑ በሚያነሡት ነጥብ ላይ መልስ በመስጠት ጊዜን ማጥፋት ለጊዜው አስፈላጊ ሆኖ አልተገኘም፡፡ ነገር ግን ይህን የሚወዛወዝ አስተምህሯቸውን ዝንባሌ መጠቆም አግባብ ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ኦርቶዶክስ መባል የለባትም

እነዚህ ወገኖች ክርስትና ማለት ሀበሾች ብቻ ተጠምቀው ይዘውት የሚገኙ ሃይማኖት አድርገው የማሰብ ያህል አጥብበው ያያሉ፡፡ የአሐቲ ቤተ ክርስቲያን እሳቤ የሌላቸውና ለሁሉም ወገን የተሰጠች መሆኗን በመዘንጋት “ተዋሕዶ ብቻ ነን” ይላሉ፡፡ ኦርቶዶክስ መባልን ሲኮንኑ ከኒቅያ ጉባኤ ጀምሮ ያሉ ሊቃው ንትን ከዚያም ለብዙ ምዕተ ዓመታት የነበሩ ሊቃውንትና ምእመናንን አኀት አብያተ ክርስቲያናትን ወዘተ እየኮነኑ መሆኑን እንኳ አላስተዋሉም፡፡ ሃይማኖታችን አንዲት/one/ ኩላዊት/catholic/ ሐዋርያዊት /apostolic/ ቅድስት /holy/ መሆኗን አያውቁም ወይም ብለን እንደምናስተምር ስናስተምርም እንደኖርን ረስተዋል፡፡

የጌታችን የመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ተቀብ ለው የቅዱሳን ሐዋርያትን ትምህርትና ትውፊት የተቀበሉ፣ ያቆዩ፣ ያጸኑ፣ በኒቅያ፣ በቁስጥንጥንያ፣ በኤፌሶን የተደረጉ መንፈ ሳዊ ጉባኤያትን የተቀበሉ፣ ሐዋርያዊ ውርስ ያላቸው፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረውን ምስጢረ ሥላሴ፣ ምሥጢረ ሥጋዌ፣ ምሥጢረ ጥምቀት፣ ምስጢረ ቁርባንና ምስጢረ ትንሣኤ ሙታን ትምህርትን እነርሱም የሚያስተምሩ አኅት አብያተ ክርስቲያናትን ሁሉ ኦርቶዶክስ እንደሚባሉ ማወቅ መረዳት ያለመቻልና ክርስትናን ከብሔርተኛ ስሜት /nationalism/ አስተሳሰብ ጋር አቆራኝተው ማየታቸው ነው፡፡

እነዚህ ሰዎች ይህን ለማለት እንደመነሻ የሚያሳብቡት “የቅባት እምነት ተከታይ የሆኑ ካህናት በጎጃም አሉ፤ ዘጠኝ መለኮት የሚሉ በዋልድባ አሉ የሚልና ተሸፍነው የሚኖሩት በኦርቶዶክስ ስም ነውና ኦርቶዶክስ የሚለውን አንቀበልም” የሚል ነው፡፡ እነዚህን አለመቀበላቸው መልካም ነው፡፡ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ሲታገሏቸው እንደኖሩ አሁንም ያንንኑ መንገድ ተከትለው ቢታገሉ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን ጥያቄው ያ አይደለም፡፡ እነዚህ ሰዎች ቤተ ክርስቲያኒቱ የምትጠራበት ስም በራሱ ከእነዚህ የኑፋቄ ወገኖች የተለየች ሆና “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን” ተብላ እንደሆነ እያወቁ “ተዋሕዶ” መባል አለብን የሚል ጉንጭ አልፋ ክርክር ያነሣሉ፡፡ “ተዋሕዶ” የሆነውን እኛን መልሰው “ተዋሕዶ እንሁን” ሲሉን ነገር እንዳለው ሁሉም ወገን መገንዘብ ይገባዋል፡፡ “ተዋሕዶ ነን” ብለን በይፋ የምንጠራበት ስም ካለን፣ ቅባትና ዘጠኝ መለኮትን የሚያነሣ መጠሪያ ከሌለን፣ በእምነትም ተዋሕዶ እምነትን እንደ ምንከተል ከታወቀ የሚፈለገው ምንድነው፡፡ ከዚህ ከሚያነሡት ክርክር ጋር ኦርቶዶክስ መባልንስ የሚያስጥል ምን መነሻ አለ፡፡

ኦርቶዶክሳዊነት እጅግ በስፋት ተተንትኖ መታየት የሚችል ለእውነተኛዋ ቤተ ክርስቲያን የተገባ ስም መሆኑን ማሳየት ቢቻልም በዚህ ጽሑፍ ማሳወቅ የተፈለገው ግን የእነዚህ ወገኖች የአለማወቅ ደረጃ በዚህ ላይ ያለ መሆኑን ነው፡፡ ኦርቶዶክስ መባልን ደባ ነው፣ ሸክም ነው ወዘተ እያሉ መለፈፋቸው ብዙ እርምጃ የማያስኬድ መሆኑን አውቀው ሊታረሙበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ “ኦርቶዶክስ” የሚለውን ቃል መለካውያን ተጠቅመውበታል ይላሉ፡፡ እነርሱ በመጠቀማቸውም እኛ እንድንጥለው ይመክሩናል፡፡ እነርሱ ክርስቲያን ተብለው እንደሚጠሩ ቤተክርስቲያን ብለው እንደሚጠሩም መገንዘብ አልቻሉም፡፡ ስለዚህ ቆይተው ደግሞ እነርሱ ክርስቲያን ተብለው ተጠርተዋልና እኛ ክርስቲያን መባልን እንድንተው፣ ቤተ ክርስቲያን መባልን እንድናስቀር ሊመክሩን ይነሣሉ ማለት ነው፡፡ ለዚህ ነው ሐሳባቸው የአይሁዳዊነት እርሾ አለው የምንለው፡፡

ስም አጠራራችን “አይሁዳዊ” የሚል ነው

እነዚህ ወገኖች ኦርቶዶክሳዊ መባልን ኮንነው ሲያበቁ ሊያሻግሩን የሚጥሩት አይሁዳዊ ወደሚለው መጠሪያ ነው፡፡ ለማስተማር ብለው በበተኑት ወረቀት ላይ ”አይሁዳዊ የሚለውን የጌታን የእመቤታችንን የንጹሐን ኢትዮጵያውያንን የከበረ ስም አጠራር ለዐመፀኛ አሕዛብ አሳልፎ መስጠት ፈጽሞ አይገባም ነበር” ይላሉ፡፡ ኦርቶዶክሳዊ ከሚለው የክርስቲያኖች ስም ሲነጥሉን ያልራሩ ሰዎች በስያሜ ከአይሁድ ጋር ተቀራረቡ በማለት ጭካኔያቸው ሲያይል ያሳዩናል፡፡ ኦርቶዶክሳዊነት የክርስትና ስም ነው፡፡ አይሁዳዊ፣ ግሪክ፣ ኢትዮጵያዊ ወዘተ የሚለው ግን የወገን፣ የብሔር ስም መሆኑን እንኳን አላስተዋሉም፡፡ ለዚህ ነው ዝንባሌው ወደ ጸሐፍት ፈሪሳውያን እርሾ ነው የምንለው፡፡

ሰንበተ አይሁድ እንጂ ሰንበተ ክርስቲያን እሑድ የሚባል የለም

እነዚህ ወገኖች የተረፈ አይሁዳውያን ትምህርት አላቸው ስንል ለዝንባሌያቸው ሌላው መነሻ ስለ ሰንበተ ክርስቲያን መስማት አለመፈለጋቸውና ሰንበተ አይሁድ እንድትነግሥ ማነሣሣታቸው ነው፡፡ “ብዙዎች በየዋሕነት ጌታ ያዘዘው ሐዋርያት የደነገጉት ነው ብለው ዕለተ እሑድን ሰንበት ነች እያሉ እንደሚያስቡ ይታወቃል፤ ነገር ግን እሑድ መቼ እነማን ለምን ዓላማ ሰንበት ተብላ ልትሰየም ቻለች ብለን ስንመረምር የሰይጣንን ተንኮል እናስተውላለን…” እያሉ እሑድ ሰንበት መባሏን የሰይጣን ሥራ ያደርጉታል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበተ አይሁድን ቀዳሚት ሰንበት ብላ እንደ ክርስትናው ሕግና ሥርዓት ተገቢውን ክብር እንደምትሰጥ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ከቅዱሳን ሐዋርያት ጀምሮ እስከ አሁን የክርስቲያን ወገን ሁሉ ሲቀድሳት የነበረችን ሰንበተ ክርስቲያንን ግን ገናና፣ ክብርት፣ ልዕልት ሆና የጌታችን መድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ ሲዘከርባት የኖረችና የምትኖር ናት፡፡ እነዚህ ወገኖች ግን የተረፈ አይሁድን ሐሳብ ዳግም ለማራገብ በመነሣት መከራከሪያ እንድትሆን ጥረት ማድረጋቸው ወደ ኋላ የሚስባቸውን አሮጌ እርሾ ያሳያል፡፡

የዳዊት ኮከብ መሠረቱ የሆነ ትእምርተ መስቀል መለያችን ይሁን

የዳዊት ኮከብ የአይሁድ ምኩራቦች መለያ ምልክት ነው፡፡ የዳዊት ኮከብ ሰሎሞናዊ እንደሆኑ በሚነገርላቸው በኢትዮጵያ ነገሥታት ዘንድ የቤተ መንግሥቱ ትእምርት ሆኖ እንደኖረ እስከ አሁን ድረስ በቤተ መንግሥትና በዩኒቨርሲቲዎቻችን አጥሮች በሚታዩት ምልክቶች እንረዳለን፡፡ ይሁን እንጂ ክርስትናውን አሽቀንጥሮ ለመጣል መሠረቱን ለመናድ ያዋሉት ሳይሆን የቤተ መንግሥቱ ምልክት ሆኖ የመንግሥቱን የትመጣ ለማጠየቅ የተገለገሉበት ትእምርት ነው፤ ከዚህ ባለፈ ግን እኛ ሁላችን ከዳንበት ከጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀሉ ትእምርት ጋር ቁርኝት የምንፈጥርበት አይደለም፡፡ ስለዚህ እነዚህ ወገኖች አሁንም ክርስትናችንን ከአይሁዳዊነት ጋር የመቀላቀል አሳብ ወይም ሌላ በሃይማኖት ስም ሊተክሉ የሚፈልጉት የፖለቲካ ርእዮት አለ ማለት ነው፡፡ እኛ ሃይማኖታችን ትእምርት የሚያደርገው የዳዊትን ኮከብ ሳይሆን ዳዊትን ጨምሮ ሰዎች ሁሉ የዳኑበትን የክርስቶስን መስቀል መሆኑን በመረዳት ሊታረሙ ይገባል፡፡

በሌላም በኩል “ቶ” እንደ ብቸኛ የመስቀል ምልክት አድርጎ ለመጠቀምና በዳዊት ኮከብ ምልክት ላይ ተቀጽሎ እንዲቀርብ ይሰብካሉ፡፡ በአልባሳቶቻቸው አትመው ወይም ቀርጸው ያሳያሉ፡፡ የ “ቶ” ቅርጽ በተለያዩ ዘመናት በተለያዩ የክርስቲያን ማኅበረሰቦች እንደሚታየው በሆነ ዘመንና ሁኔታ ወስጥ የመስቀል ምልክት ሆኖ አገልግሎ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚያ በመለስ ግን የሆነ የቤተ ክርስቲያናችን መለያ እንዲሆን አድርጎ የመቀሰቀስ ሥልጣን ግን ለዚህ ቡድን የሰጠው የለም፡፡ ካልሆነ ግን የሚኖረው ፋይዳ በእነ ዴርቶጋዳ፣ ራማቶሐራ፣ ዣንቶዣራ ከሚነገረን ልቦለዳዊ የርእዮተ ዓለም መግባቢያነት ያለፈ አይሆንም፡፡ በዚያም ልቦለዳዊ ታሪክ እንኳ ቢሆን ይህን የምስጢር መልእክት መቀባበያ አድርጎ ሲጠቀምበት የነበረው ገጸ ባህርይ በቤተ ክርስቲያን ስም የሚኖር አባ ፊንሐንስ የተባለ የይሁዲ እምነት ተከታይ ነበር፡፡ ታሪኩን ስናነብ የሌላዋን ገጸ ባሕርይ የልጁን የሲጳራን ክርስቲያናዊ ሕይወት ለማስጣል የአንገቷን መስቀል ለመበጠስ ሲታገል የነበረ አስመሳይ መነኩሴ ነው፡፡ በዚህ ታሪክ ወስጥ ታዲያ “ቶ” የዚህ አስመሳይ መጠቀሚያ ነበር፡፡ ታዲያ እነዚህ በእውኑ ዓለም ያሉ ወገኖች “ቶ”ን ካልተጠቀመን ሞተን እንገኛለን ሲሉ በክርስትና ስም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እየኖሩ የራሳቸውን ተልእኮ ለማሳካት የሚሮጡ ተረፈ አይሁዳውያን ናቸው አያስብል ይሆን!

ዮዲት ጉዲት ስሟ ታሪኳ ተዛብቷል

“ደቂቀ ኤልያስ” ብለው ራሳቸውን የሚጠሩት እነዚህ ወገኖች አይሁዳዊ እንደሆነች ታሪክ የጻፈላትን ዮዲት ወይም ጉዲት ወይም እሳቶ የሠራችውን ሥራ እንደበጎ ተቆጥሮ ታሪክ እንዲገለበጥ ይሠራሉ፡፡ ዮዲት ጉዲት አብያተ ክርስቲያናትን ስታጠፋ ክርስቲያኖችን ስታርድ መኖሯን ታሪክ እየመሰከረ ነቢዩ ኤልያስ ነገረን በሚል ማስረጃ እውነታው ተገልብጦ ጠንቋዮችን ዐመፀኛ ካህናትን ወዘተ እንዳጠፋች እንዲታሰብ ሊያግባቡን ይጥራሉ፡፡ ሰልፋቸው የአይሁድን ገጽታ የመገንባት ከተቻለም ከይሁዲነት የሃይማኖት እሳቤዎች እየሸራረፉ ለማጉረስ በመሆኑ እንቅስቃሴው የተረፈ አይሁድ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መዋቅር በአውሬው መንፈስ የሚመራ ነው

እነዚህ ወገኖች ያዘሉት ጭፍንነት የተሞላበት አካሔድ በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያኒቱን እንደሚጠሏት ያሳብቃል፡፡ በታሪክ ረገድ ከንግሥተ ሳባ እስከ ደቂቀ እስጢፋ፣ በአስተዳደር ዘማዊና መናፍቅ ከሚሏቸው ጳጳሳት እስከ ሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ በሃይማኖት ከኦርቶዶክስ አይደለንም እስከ ሰንበተ ክርስቲያንን መሻር ድረስ የተመሰቃቀለ መሠረት የለሽ ቅዠትን ይዘው ተከታይ ለማፍራት መንቀሳቀሳቸው፣ ሊያውም በቤተ ክርስቲያኒቷ ውስጥ መሆኑ ለሃይማኖት ቤተሰቡ ያላቸውን ንቀትና የድፍረት አሠራራቸውን ያስረዳል፡፡ ስለዚህ ሲቀሰቅሱም ቤተ ክርስቲያኒቱ እንደፈረሰች አደርገው ነው፡፡ ለዚህም “የኢትዮጰያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተባለው መዋቅር ማንንም ሊደግፍና ሊጠልል ቀርቶ እራሱን እንኳን ማቆም ያልቻለ በገዛ ራሱ የፈረሰ የእንቧይ ካብ መሆኑን እንረዳለን” ይሉናል፡፡ ተስፋ ማስቆረጥ ይፈልጋሉ፤ መንጋውን መበተን ይሻሉ፤ ለማን ሊሰጡት እንደሆነ አይታወቅም፤ ግን ምእመኑ እንዲሸሽ ይመክራሉ፡፡ የሆነውም ያልሆነውም በካህናትና መነኮሳት ተሠሩ የሚሏቸውን የሥነ ምግባር ችግሮች መቀስቀሻ ያደርጉታል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ አስተዳደራዊ ችግሮችን የሃይማኖታዊ አስተምህሮ ችግር ያህል አድርገው ይሰብካሉ፡፡ በእነርሱ እሳቤ የቤተ ክርስቲያኒቱ ዲያቆናት ቀሳውስት ጳጳሳትም ሁሉ የቅባት፣ የዘጠኝ መለኮት ወልድ ፍጡር የሚሉ አሪዮሳውያን ወዘተ ኑፋቄ ተከታዮች ናቸው፡፡ ስለዚህ ከእነርሱ መስቀል መሳለም፣ በእነርሱ እጅ መቁ ረብ የማይገባ ነው፡፡ ስለዚህ ቤተ ክህነቱ መንጋውን እንዲሰበስብ አይፈልጉም፡፡

ቤተ ክህነቱ መንጋውን መሰብሰብ እንዳይችል ሆነ ማለት የክህነትን ሥልጣን እንደሌሎች መናፍቃን ካድን ማለት ነው፡፡ እንደውም በኢትዮጵያዊው መልከጼዴቅ ሥርዓተ ክህነት የሆነ አዲስ ሊቀካህን ይኖርና ክህነት እንደ አዲስ ኤልያስ ለመረጣቸው ይሰጣል፤ ይላሉ፡፡ ልብ በሉ “ሊቀ ካህን” የሚለው እሳቤ ዳግም ወደ አይሁድ ዓለም የሚስብ ነው፡፡ ለአንዳንዶችም መስቀል ከሰማይ እንደተላከ ሆኖ ሲሰጣቸው የታየበት መድረክም አለ፡፡ ስለዚህ በእነሱ እሳቤ ሐዋርያዊ ውርስ የሚባል ነገር በክህነት አይታሰብም፡፡ ስለዚህ ክህነቱ ተክዷል፡፡ ይህንን ካላመንን ደግሞ የሚያጠምቀን የሚያቆርበን የሚናዝዘን የሚያመነኩሰን የሚያጋባን የሚፈውሰን በቅብዐ ሜሮን ለእግዚአብሔር የሚለየን ማን ይሆናል፡፡ እንዳትቆርቡ ብለው ሲቀሰቅሱ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ እየለዩን ነው፡፡ ስለዚህ እርሱን እንዳንቀበል የሚሠ ሩትስ ለምንድነው፡፡ ካህን ከግብጽ ይመጣል እንዳይሉን ግብፆችም ለእነዚህ ወገኖች መሰሪና ተንኮለኞች ናቸው፡፡

“ካህናቱ የበኣል የጣዖት ካህናት ሆነዋልና አትቀበሏቸው” በሚለው በእነዚህ ሰዎች ልፈፋ የሚከሰሰው ሁሉም ከሆነ ቤተ ክርስቲያኒቱ ያለችው ከእነማን ጋር ነው፡፡ ማኅበራቱ፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶቹ ሁሉ በዚህ ቡድን እሳቤ የአውሬው ወገኖች ናቸውና፡፡ ታዲያ ያለክህነት እና ካህናት ያለ አገልጋይ መምህራን ሰባክያነ ወንጌል የምትኖር የተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንዴት ያለች ናት፡፡ ስለዚህ ያላችሁት ያለሰብሳቢ ነው እያሉን ነው፡፡ ታዲያ የሚፈልጉት እንድንበተን ብቻ ከሆነ “ደቀ መዛሙርቱ ሰርቀውታል እንጂ አልተነሣም” እያሉ በክርስቶስ አምነው የነበሩትን ክርስቲያኖች ተስፋ አስቆርጠው ሊበትኑ ከተነሡት አይሁድ አሠራር በምን ይለያል፡፡ መንገዳቸው ቅስቀሳቸው ሁሉ የማፍረስና የጭካኔ ነውና፡፡

ከመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ከዓለም አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት እንለይ

ለእነዚህ ወገኖች በክርስትና ስም ካሉ ከሁሉም ወገኖች ጋር መጎራበታችንን አይወዱም፡፡ ስለዚህ ከሃምሳ ዓመታት ያላነሰ የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያነቡ ለማድረግ አስተርጉሞ አሳትሞ በማከፋፈል አገልግሎት እየሰጠ ያለውንና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም በዋናነት ተሳትፎ ከምታደርግበት ማኅበር እንድንርቅ ይመክራል፡፡ ሰዎችን ያነሣሣል፡፡ እነርሱን ጨምሮ ብዙዎች በሀገራችን በአማርኛና በሌሎችም ቋንቋዎች ተተርጉመው የቀረቡ መጻሕፍት በቀላሉ ማግኘት እንዲቻል ድጋፍ እየሰጠ ያለውን ማኅበር የጥፋት መልእክተኛ ማድረግ ሚዛናዊነት የጎደለው ብቻ ሳይሆን የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ስልታዊ በሆነ መልኩ የማዳከም ፍላጎት ነው፡፡

በመሠረቱ እነዚህ ወገኖች የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበርን ብቻ ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስን የእምነት መሠረት ማድረግን የሚቀበሉ አይደሉም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ቃሉ በተንኮልና በአውሬው አሠራር ተለውጧል ብለው ያስባሉ፡፡ የዚህ ምክንያት ግን ግልጽ ነው እነርሱ ለሚነዟቸው ልፍለፋዎች ሁሉ ደጋፊ የሚያደርጉት መጽሐፋዊ መነሻ አለመኖሩ ነው፡፡ ስለዚህ ሲመቻቸው “በመጽሐፍ ቅዱስ የተነገረው የዓለም የፍጻሜ ዘመን ተቃርቧል” ይላሉ፤ ሳያስፈልጋቸው ደግሞ “መጽሐፍ ቅዱስና መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበርን አትመኑ” እያሉ ይቀሰቅሳሉ፡፡ ለእነርሱ ታማኙ የእምነታቸው መጽሐፍ “የኤልያስ ዐዋጅ ነው” የሚሉት በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የሚሠራውን ደባ እያቀነባበረ ያለው የእነርሱ “አባትዬ” ተራ ድርሰት ነው፡፡ እርሱ ለዘመናት ተሻግሮ ከመጣው ቃለ እግዚአብሔር በላይ ታማኝ ነው፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን ያስጥላል፡፡

ከዚህም ተሻግሮ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት አባል መሆን ገንዘብ መውደድ እንደሆነ አድርጎ አጥብቦ ለማሳሰብ ይሠራሉ፡፡ ከኅብረቱ ወጥቶ እነርሱን መሳብ እንጂ መተባበር ሃይማኖት ያጠፋል ብለው ያስባሉ፡፡ ሃይማኖትን ማስፋፋት ከማይፈቅዱ ወገኖች ጋር ቤተ ክርስቲያን የተባበረች አድርጎ በማሳሰብ የክርስትና ሽታ ካላቸው ኦርቶዶክስ የሚባሉ አኀት አብያተ ክርስቲያናትን ጨምሮ ቤተ ክርስቲያን አጠገባቸው እንድትደርስ አይሹም፡፡ ክርስትናን መሸሹ እንዳለ ሆኖ እንድንጠነቀቅ ከማሳሰብ የሚነሣ ሳይሆን አጠገባቸው እንዳንደርስ በፍርሃትና በጥርጣሬ ተሞልተን፣ ራሳችንን ብቻ አጽድቀን እንድንነሣ ስለሚገፉ አካሔዱ አይሁዳዊ እርሾ የተቆራኘው ነው፡፡ ሌላውን የኃጢአት ጎተራ አድርጎ ከመፍረድ ያልፍና አይሁድ ጌታን በሚከሱበት “የአብሮ በላ አብሮ ጠጣ” ክስ ቤተ ክርስቲያንንም ሊከሱ ይነሣሉ፡፡

ሰንበት ትምህርት ቤቶች አያስፈልጉም

እነዚህ ወገኖች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ለማዳከም የሚሠሩ ሤረኞች መሆናቸውን በቀላሉ የምንረዳው በዚህ ዘመን ያሉ የቤተ ክርስቲያንን የአገልግሎት ምሰሶዎች ለመነቅነቅ መቋመጣቸው ነው፡፡ ለዚህ ማሳያው ሰንበት ትምህርት ቤቶችን በማመስገን ፈንታ ሲወቅሷቸው፣ በማበረታታት ፈንታ ሲሰደቧቸው መታየታቸው ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች በረጩት ጽሑፍ ላይ ያስነበቡንን ስናይ “ሰንበት ትምህርት ቤት አውሬው የቤተ ክርስቲያን ልጆችን ለማጥመድ የመሠረተው ረቂቅ ስውር ወጥመድ ነው” ይላሉ፡፡ ሴቶችን ከሊቃውንት በላይ አድርጎ ወረብ ያስወርባል፤ የአውሮፓ ባህል ነው፣ አስነዋሪ ሥራዎች ይሠሩበታል…ወዘተ እያሉ ተራና ጽንፈኛ ቅስቀሳ ያደርጋሉ፡፡ ይህ ክርስትናን ሃይማኖቴ ነው ብሎ ከሚከተል ወገን የሚሰነዘር አይደለም፡፡

ሰንበት ትምህርት ቤቶች ምእመናንን ከመናፍቃን ለመጠበቅ የሠሩትን፣ ሕፃናትና ወጣቶች ቤተ ክርስቲያንን እንዲያውቋት፣ የፈጸሙትን አገልግሎትና ቤተ ክርስቲያንም የአገልግሎት ውጤቱን አይታ አንድ መምሪያ ያቋቋመችለት መሆኑን እያወቁ፤ ካላቸው የተረፈ አይሁዳዊነት ስውር ተልእኮ አንጻር ሰንበት ትምህርት ቤቶች በሠሩት አገልግሎት ተቆጥተው የሚያስተጋቡት ስም ማጥፋት ነው፡፡ አካሔዳቸው ፀረ ስብከተ ወንጌል ነው፤ ስለዚህ ፀረ ክርስትና ነው፤ ስለዚህም የአይሁድ ቅናትን ያዘለ ነው፡፡

ኤልያስ መጥቷል

ኤልያስ ከብሔረ ሕያዋን መምጣቱንም ሊያበስሩን ይሞክራሉ፡፡ አስገራሚው ነገር ከላይ የተነሡ ሁሉንም ጉዳዮች የገለጠው ያወጀው የፈረጀው የለወጠው የሻረው ያጸደቀው የኮነነው ነቢዩ ኤልያስ እንደሆነ በየምዕራፉ ይነግሩናል፡፡

ነቢዩ ኤልያስና ሄኖክ በመጽሐፍ ቅዱስ ቃል መሠረት በምድር ላይ እንደሰው ተመላልሰው በኋላ ግን ሞትን ሳይቀምሱ በማረግና በመሰወር በብሔረ ሕያዋን እስከ አሁን እንደሚኖሩ ይታመናል፡፡ ሰው ሆኖ ተፈጥሮ በለበሱት ሥጋ መሞት ለማንም አይቀርምና ወደዚህ ዓለም መጥተው በሰማዕትነት እንደሚያርፉ የቤተ ክርስቲያናችን ነገረ ሃይማኖት ያትታል፡፡ ከዚያም በመነሣት ስለኤልያስ መምጣት የተነገሩባቸው ሁለት የትንቢት ቃሎች በመጽሐፍ ቅዱሳችን አሉ፡፡ የመጀመሪያው ከመሲሑ ከክርስቶስ መምጣት አስቀድሞ እንደሚመጣ የተነገረው ምጽአት ነው፡፡ ይህም በነቢዩ ሚልክያስ “እነሆ ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ ነቢዩን ኤልያስን እልክላችኋለሁ፡፡ መጥቼም ምድርን በእርግማን እንዳልመታ እርሱ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች የልጆችንም ልብ ወደ አባቶች ይመልሳል፡፡” ተብሎ የተነገረው ነው /ሚል. 4፥5/፡፡

ሌላው የትንቢት ቃል ደግሞ በዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ ላይ የተነገረው የሚከተለው የትንቢት ቃል የተተረጎመበት ክፍል ነው፡፡ “ለሁለቱም ምስክሮቼ ማቅ ለብሰው ሺሕ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን ትንቢት ሊናገሩ እሰጣለሁ፡፡ እነዚህ በምድር ጌታ ፊት የሚቆሙ ሁለቱ ወይራዎችና ሁለቱ መቅረዞች ናቸው፡፡ ማንምም ሊጎዳቸው ቢወድ እሳት ከአፋቸው ይወጣል፡፡ ጠላቶቻ ቸውንም ይበላል፡፡ ማንም ሊጎዳቸው ቢወድም እንዲሁ ሊገደል ይገባዋል፡፡ እነዚህ ትንቢት በሚናገሩበት ወራት ዝናብ እንዳ ይዘንብ ሰማይን ሊዘጉ ሥልጣን አላቸው፤ ውኃዎችንም ወደደም ሊለውጡ በሚፈልጉበትም ጊዜ ሁሉ በመቅሰፍት ሁሉ ምድርን ሊመቱ ሥልጣን አላቸው፡፡ ምስክራቸውን ከፈጸሙ በኋላ ከጥልቁ የሚወጣው አውሬ ይዋጋቸዋል፤ ያሸንፋቸውማል፡፡ ይገድላቸውማል፡፡ በድናቸውም በታላቂቱ ከተማ አደባባይ ይተኛል፡፡ እርሷም በመንፈሳዊ ምሳሌ ሰዶምና ግብፅ የተባለች ደግሞ ጌታቸው የተሰቀለባት ናት፡፡ ከወገኖችና ከነገዶችም ከቋንቋዎችም ከአሕዛብም የሆኑ ሰዎች ሦስት ቀን ተኩል በድናቸውን ይመለከታሉ፡፡ በድናቸውም ወደ መቃብር ሊገባ አይፈቅዱም እነዚህ ሁለት ነቢያት በምድር የሚኖሩትን ስለ ሣቀዩ በምድር የሚኖሩት በእነርሱ ላይ ደስ ይላቸዋል፡፡ በደስታም ይኖራሉ እርስ በእርሳቸውም ስጦታ ይሰጣጣሉ፤ ከሦስት ቀን ተኩልም በኋላ ከእግዚአብሔር የወጣ የሕይወት መንፈስ ገባባቸው፤ በእግሮቻቸውም ቆሙ፡፡ ታላቅም ፍርሐት በሚመለከቱት ላይ ወደቀባቸው፤ በሰማይም ወደዚህ ውጡ የሚላቸውን ታላቅ ድምፅ ሰሙ፡፡ ጠላቶቻቸውም እየተመለከቷቸው ወደ ሰማይ በደመና ወጡ፡፡…” /ራእ. 11፥3-03/ በዚህ ቃለ እግዚአብሔር ውስጥ “ሁለቱ ምስክሮቼ”፣ “ሁለቱ ወይራዎች”፣ “ሁለቱ መቅረዞች”፣ “ሁለት ነቢያት” እያለ የሚጠራቸው በዚህ ዓለም ሞትን ያልቀመሱ ሁለቱ የእግዚአብሔር ወዳጆች ሄኖክና ኤልያስ እንደሆኑ ሊቃውንቱ በትርጓሜ ያስቀምጣሉ፡፡ እነዚህም ቅዱሳን የሚገለጹት ከጥልቁ የሚወጣውን አውሬ ሊዋጉ ነው እንጂ ቤተ ክርስቲያንን ሊዋጉ አይደለም፡፡

እነዚህ ከላይ የተጠቀሱ ትንቢቶች ትንቢት እንደመሆናቸው መጠን የተፈጸሙበትን ጊዜና ሁኔታ ሊረዱ የሚችሉት ቅዱሳን ናቸው፡፡ “በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም” /2ጴጥ.1፥21/ እንደተባለ በሥጋና ደም ሰዎች የሚረዷቸው አይደሉም፡፡ ይህ አካሔድ አይሁድን ከሃይማኖት መንገድ ያስወጣቸው ነው፡፡

አይሁድ በኤልያስ መምጣት ጉዳይም ስተዋልና፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ለጌታችን “እንግዲህ ጻፎች ኤልያስ አስቀድሞ ሊመጣ ይገባዋል ስለምን ይላሉ ብለው ጠየቁት” የነቢያት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው “ኤልያስማ አስቀድሞ ይመጣል ሁሉንም ያቀናል፤ ነገር ግን እላችኋለሁ ኤልያስ ከዚህ በፊት መጣ የወደዱትንም ሁሉ አደረጉበት እንጂ አላወቁትም” አላቸው፡፡ ስለ መጥምቁ ዮሐንስ እንደነገራቸው አስተዋሉ፡፡/ማቴ.17፥11/ አይሁድ ግን በሥጋና ደም ለትንቢቱ ትርጓሜ አበጅተው ይጠባበቁ ነበር፡፡ በግብሩ፣ በመንፈሱ፣ በአኗኗሩ ኤልያስን መስሎ ንስሐ ግቡ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኸው ድምፅ ኤልያስ የተባለው ዮሐንስ መሆኑን አላስተዋሉምና እርሱንም መሲሁንም ሳይቀበሉ ቀሩ፡፡ ለዚህም ነው እንዲህ ያለው አስተሳሰብ የአይሁድ በመሆኑ የአሁኖቹ “ኤልያሳውያን” አካሔድ ተረፈ አይሁዳዊነት ነው የምንለው፡፡

በአንድ በኩል ይህንን የነቢዩ ሚልክያስን ቃል ይዘው እየሞገቱን ከሆነ ዮሐንስ መጥምቅን በኤልያስ መንፈስ መምጣቱን አለመቀበልና ብሎም መሲሁን ኢየሱስ ክርስቶስንም እንዳለመቀበል ነው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ነገ ከነገወዲያ ባለፉት ዓመታት በየአደባባዩ ስታውከን እንደነበረችው ሴት መሲሁ ተወልዷል ወይም ሊወለድ ነው ሊሉን ተዘጋጅተዋል ማለት ነው፡፡ ይህ በግልፅ የመጣ የይሁዲ እምነት አራማጅነት ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በዮሐንስ ራእይ የተቀመጠውን የትንቢት ቃል መነሻ አድርገው እየሞገቱን ከሆነ ደግሞ አስተሳሰቡ አሁንም ትንቢትን ለገዛ ራስ መተርጎም እንዳይሆን ልንጠነቀቅበት የሚገባ ነው፡፡ ለገዛ ራስ መተርጎም የጸሐፍት ፈሪሳውያን እርሾ ነው፡፡ የእነዚህ ሰዎች አካሔድ ሃይማኖትን ተራ ጨዋታ ወደ ማድረግ የሚወስድ ነው፡፡ ሃይማኖትን በንቀት እንዲታይ የማራከስ አካሔድ ነው፡፡ ኤልያስ መጥቷልና አጅቡት ተቀበሉት እያሉ በየመንደሩ መቀስቀስ እገሌን ይጥላል እገሌን ያፈርሳል እያሉ በማውራት ለምእመናንን ምልክት ፈላጊነትን ማለማመድ ነው፡፡ ሰዎች ሃይማኖት ከምግባር ይዘው እንዲገኙ ከማስተማር ይልቅ ኤልያስን ፈልጉት እያሉ ማባዘን ተገቢ አይሆንም፡፡ ይህ “የአመንዝራ ትውልድ” ጠባይ ነው፡፡ ምልክትን የሚፈልግ ማኅበረሰብ እምነትን ይዞ ለመገኘት አይቻለውም፡፡

እነዚህ ወገኖች አሳባቸው ሥጋዊ ስለሆነ የትንቢቱን መፈጸም ሊነግሩን የሚቻላቸው አይደሉም ሊባል የሚችልበት ምክንያት አለ፡፡ ለእነዚህ ሰዎች ኤልያስ የሚመጣው የአትዮጵያን ቤተክህነት አፍርሶ ሊያድስ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ቤተ መንግሥት ሊያስተካክል ነው፡፡ ባንዲራውን ከአረንጓዴ ቢጫ ቀይም አልፎ በሰባቱ የቀስተ ደመና ረቂቅ ቀለማት /spectrum/ አስውቦ ሊተክል ነው፡፡ የኢትዮጵያን ታሪክ እየከለሰ ሊያስጠናን ነው፡፡ ስብከተ ወንጌል የሚያካሒዱ ሰንበት ትምህርት ቤቶችና ማኅበራትን ሊያፈርስ ነው፡፡ ሰንበትን ሊሽር ወይም ሊተካ ነው፡፡ ነግሦ የኢትዮጵያን ሕዳሴ ሊያመጣ ነው፡፡ ይህ ፍጹም ብሔርተኛና ፍጹም ሥጋዊ የሆኑ ሐሳቦች ናቸው፡፡ ካልሆነም የጥንቆላና የመናፍስት ሥራ ነው፡፡ ካልሆነም ለሥጋዊ ጥቅም የሚደረግ ሩጫ ነው፡፡ ካልሆነም ብዙዎች እንደሞከሩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ለመፈታተን የመጣ ሌላ አዲስ የዘመቻ ጽንፍ ነው፡፡ በስሕተትም ቢሆን ግን ስሕተቱ ትንቢትን ለገዛ ራስ የመተርጎም ዝንባሌ ነውና ተረፈ አይሁዳዊነት ነው፡፡

ማጠቃለያ

እነዚህ ወገኖች ያነሧቸው የማሳሰቻ ቅስቀሳዎች በራሳቸው የትም የማያደርሱ የተሰነካከሉ ሐሳቦች ቢሆኑም ፀጉሩን የገመደ፣ ቆዳ የለበሰ፣ ባዶ እግሩን የሚታይ “ባሕታዊ” አንድ መዓዝን ላይ ሲጮኽ አይተው ቆመው ለሚሰሙ የዋሐን ግን ጥርጥርና ማደናገሪያ ማሳቻ መሆኑ አይቀርም፡፡ ቡድኑ ከዚህ አልፎ በሕዝብ ዘንድ ይታወቃሉ የሚላቸውን አንዳንድ የዋሕ አርቲስቶች ቀስቃሽ ለማድረግ እንደ ስልት መያዙ ደግሞ የምር ታስቦበት ለመዝመት እየተሠራ መሆኑን ያሳያል፡፡

እነዚህ ወገኖች በየዓለሙ መዓዝን ዓለም ሊጠፋ ነው ብለው እንደሚቀሰቅሱት ምጽአት ናፋቂዎች ናቸው ብሎ ደፍሮ ለማውራትም የማይመች ነው፡፡ የሚያወሩልን ስለፍፃሜ ዓለምም አይደለም፤ ኢትዮጵያ በኤልያስ ገና ወደ ልዕልና እንደ ምትመጣ፣ በረከት መልካም ዘመን እንደሚቀርብ ሊነግሩን ነው፡፡ ስለዚህ ስለነገረ ምጽአት የሚነግሩን ከሆነ ምጽአት ናፋቂዎች ብለን ልንፈርጃቸው በቻልን፤ ነገር ግን ኤልያስን የሚፈልጉት አይሁድ የክርስቶስን መወለድ ለሚፈልጉበት ለሥጋቸው፣ በዓለሙ ላለ ልዕልናቸው ነው፡፡ የሀገርን ክብርና ልዕልና መመኘት መልካም ነው፤ ነገር ግን በሃይማኖት ስም ሰዎችን እያስጎመጁ እያማለሉ ከመንገዳቸው ማሳት ግን ነውር ነው፡፡

የቅዱሳንን ስም የሚያከብረው የኢትዮጵያ ክርስቲያን ወገን በቅዱስ ኤልያስ ስም የመጡ እነዚህን ስዱዳን ማንነት እንዲረዳ ያስፈልጋል፡፡ “ደቂቀ የሎስ” ሆነው የደካሞችን ነፍስ ሊነጥቁ መምጣታቸውን ማስገንዘብ አለብን፡፡ ከተቻለ ሁሉንም ማረምና ማስተካከል የቤተ ክርስቲያን ወገኖች ድርሻ ሊሆን ይገባል፡፡ ካልሆነ በዓላማ ለጥፋት እየሠሩ ካሉት ደበኞች የዋሐኑን መለየት ተገቢ ይሆናል፡፡ አስቀድመን በጽሑፉ መግቢያ ያነሣናት አሳች ሴት እንኳ ለረጅም ጊዜ በማሳቷ ጸንታ ምእመናንን ግራ ስታጋባ መቆየቷ ይታወቃል፡፡ ይህም እንቅስቃሴ ይህቺ ሴት ባደረገችው መንገድ የመናፍስትና የጥንቆላ አሠራር አብሮ እየታከለበት ከሔደ ደግሞ ነገሩ ውስብስብ ስለሚሆን ካሁኑ ሁሉም ወገን የድርሻውን ተወጥቶ በእንጭጩ መቅጨት ይገባል፡፡

 
‹‹ ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናል›› 1ጴ 4፣8

‹‹ኃጢአት አንዳች የእግዚአብሔር ፀጋ፣ ሰማያዊ በረከት፣ በነፃ የተቸረን የለጋስ አምላክ ሥጦታ የማጣት ትርጉም ያለው ክፉ የመንፈስ ደዌ ነው፡፡ የዘላለሙን አምላክ ለሰው ልጆች ያለውን ዓላማ ለጊዜውም ቢሆን ያደናቀፈ፣ ልዑላዊ ክብር ተችሮት በአምላክ አምሳያ የተፈጠረውን ሰው ያዋረደ፣ የአዳምን ውበት ያጠፋ፣ የሔዋንን ደም ግባት ያረገፈ፣ የልጆቻቸውን ዕድሜ በበርካታ መቶ ዓመታት የቀነሰ ይኸው የሰው ልጆች የዕድሜ ልክ ቀበኛ ‹‹ኃጢአት›› ነው፡፡

ኃጢአት የሚበልጠው የሚሽረው እስኪመጣ ድረስ የሰዎችን ማንነት የመለወጥ ብቃት፣ የህይወት አቅጣጫን የመቀየር ብርታት፣ የዓለምን ጉዞ ወደ ፈቃዱ የማዞር አቅም ነበረው፡፡ ስለሆነም የምድር ፍጥረትን ገዢ አንገቱን አስደፍቶ በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት ገዛው፡፡ አዳም ሊነግስባትና ሊረባባት የተሰጠችውን ምድር በምልአት አፍኖ በውስጧ ያሉትን ሁሉ ነገሰባቸው፤ ረባባቸው፡፡ አዋቂውን ፍጡር አሳውሮ በድንቁርናና ባለማስተዋል ጠፍር ተብትቦ የፈጠረውን አምላክ አስረስቶ እንጨት ያስጠረበው፣ ድንጋይ ያስለዘበው፣ ብረት ያስቀለጠው ይኸው ‹‹ኃጢአት›› ነው፡፡ ‹‹በአንድ ሰው ምክንያት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ›› ሮሜ 5፣12 ተብሎ እንደተፃፈ የኃጢአት ምክንያቱ አንድ ቢሆንም ርባታው ግን በመላው የሰው ልጆች ልብ ተቀፍቆፎ በአንደበታቸው በገፃቸውና በብልቶቻቸው ሁሉ ስለተፈለፈለ ብዛቱ የምድር አሸዋና የሰማይ ከዋክብት ቢባዙና ቢበዙ የማይተካከሉት ኁልቆ መሳፍርት ከ እስከ የሌለው ሆኗል፡፡

ስለሆነም እግዚአብሔር ከሰማይ ሆኖ ሲጎበኝ ምድርና ፍጡራን ሲመለከት የደስታ አምላክ እስኪከፋው፣ በፍጡሩ እስኪያዝን፣ በሥራው እስኪፀፀት ድረስ የሚጠቀስ ሁነኛ ሰው እንዳጣ ፍርድና ፅድቅንም እንዳላገኘ ተነግሯል ኢ፡ 59፣16፡፡ የዚህን ምክንያቱ ደመና ሰማይን እንደሚሸፍን ውሃም ሸለቆን እንደሚከድን ኃጢአትም ምድርንና ምድራውያንን ውጦአቸዋልና ከፀበሉ ያልደረሰው ከምሬቱ ያልተጎነጨ ባለመኖሩ ነበር፡፡ ለዚህም ነው ‹‹ፃዲቅ የለም አንድ ስንኳ አስተዋም የለም እግዚአብሔርንም የሚፈልግ የለም፡፡

ሁሉ ተሳስተዋል በአንድነትም የማይጠቀሙ ሆነዋል፡፡ ሁሉ ኃጢአት ሰርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል›› ተብሎ የተፃፈ በሮሜ፡ 3፡11፣23፡፡ *የሚደንቀው የኃጢአት ብዛቱ ምንም መሥፈሪያና መዘርዘሪያ መመዘኛና መመጠኛ ቢታጣለት የበደል ስፍዓቱ የምድርን ክበብ ዘልቆ የህዋን ክልል ቢሸፍን አምላካዊ ፍቅር ከዚህ እጅግ በዝቶ ያለልክም ተርፎ የብዙ ብዙ የሰፊም ሰፊ የሆነውን ኃጢአት ሊወጠውና ሊሸፍነው መቻሉ ነው፡፡ የአምላካችን ፍቅሩ ከጥልቆቹ ሁሉ የጠለቀ ከአንሰርቶች ሁሉ የረዘመ ለስፋቱም የአድማስ ጥግ የሌለው በመሆኑ በእርግጥ የኃጥያትን ብዛት ይሸፍናል፡፡

የሰው ልጅ የኃጢአት ብዛት ውጦት ድምፁ በማይሰማበት፣ ጩኸቱ በማይደመጥበት ሰዓት፤ የኃጢአት ብርታት አቅም አሳንሶት፣ ጉልበት አሳጥቶች ጌታውን መከተል ባልቻለበት ጊዜያት፤ የኃጢአት ፅልመጽት ህሊናውን ጋርዶት፣ዓይኑን አሳውሮት የአምላኩን ፈቃድ መለየት በተሳነው ወቅት፤ የጭንቅ ቀን ደራሽ የሆነለት በብቃቱና በብርታቱ ከሁሉ የሚልቀው እንዲያው በነፃ የተገለፀው አምላካዊ ፍቅር ነበር፡፡ ይህንኑ ቅጥ ያጣ ማህበራዊ ኑሮ፣ የተበላሸ አስተሳሰብና በኃጢአት ቀንበር የወደወቅን ህብረተሰብ ለመታደግ ምክንያት ሊሆን የሚችል የሰው ወገን ስላልተገኘ የእግዚብሔር የገዛ ክንዱ መድኃኒት እንዳመጣለት ፅድቁም እንዳገዘው ተጠቅሷል፡፡ ‹‹በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘልዓለም ህይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና›› ዮሐ 3፣16፡፡ እንግዲህ የሰዎችን ሕይወት፣ ታሪክ፣ ስምና መንገድ የቀየረ ይህ እንዲው ተብሎ የተገለፀው ምክንያት የሌለው ፍቅር ነበር፡፡ ልጅ ተብሎ የተገለፀው ጌታ ኃያል አምላክ፣ የሰላም አለቃና የዘለዓለም አባት ተብሎም የተጠራ የዘመናት ሽማግሌ እንጂ እንደሰው ዘመንና ወራት የሚቆጠሩለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ለአባቱ የባህርይ ልጅ ነውና ልጅየውም ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው ‹‹አንድያ›› ተብሎ የተጠራ፡፡ እንደልጅነቱም የራሱም ፈቃድ የሆነውን የአባቱን ፈቃድ ሊፈፅም የሰው ልጆች ፍቅር አገብሮት እንደሰው ተገለፀ፡፡ ‹‹ፍቅር ሰሀቦ ለወልድ ኃያል እመንበሩ ወአብፅሆ እስከለሞት›› ኃያል ወልድን ፍቅር ከመንበሩ ሳበው እስከሞትም አደረሰው፡፡ አዎን! ከሰዎች አዕምሮና አቅም በላይ የሆነውን ኃጢአት በፅድቁ ያንበረከከው የእግዚአብሔር ፅድቅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ለመለኮታዊ ጌታ መገለፅ በእኛ መካከል ማደርና ስለኃጢአታችን መሞት ብቸኛው ምክንያት ወሰን የሌለው ፍቅሩ ነበር፡፡

ይህም አምላካዊ ግብር ለሰው ልጆች የአምላካቸውን ውዴታ የሚያረጋጋጡበት ጽኑ ማስረጃ ነው፡፡ ሐዋርያውም ‹‹ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለእኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል›› ሲል መስክሯል ሮሜ 5፣8 እግዚአብሔር በባህሪው ፍቅር በመሆኑ ፍቅር ወለድ አምላካዊ ሥራዎቹ እጅግ በርካታ ናቸው፡፡ ሰውን ከአለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ በምናብ እንኳ በማይታወቅበት ጊዜ በግዙፍ አካል አቁሞ በሰማይና በምድር እውቅና የሰጠው፣ ህልውና ያገኘው ማንነት የሰማያዊውን አምላክ መልክና ምሳሌ ተላብሶ ወደር ለማይገኝለት ክብር የበቃው በእግዚአብሔር ፍቅር ነበር፡፡ ይኸው ፍቅር አንድ ጊዜ የወደደውን አዳም እስከመጨረሻው በመውደድ ከእርሱ በፊት የተፈጠሩትን ከሰማይ በታች ያሉትን ፍጥረታት ሁሉ አስገዛለት፡፡ አምላካዊ ፍቅር በጊዜ፣ በቦታና በሁኔታ የማይገደብ በመሆኑ የጌታውን ፍቅር የዘነጋ ሥጦታውን ልብ ያላለው ሰው ትዕዛዝ ተላልፎ እርቃኑን በቀረ ጊዜ ፍርሃቱን በቅጠል ሊጋርድ ሲጥር ቁርበት ያለበሰው፣ ከደስታ ምድር ሲባረር እንደወጣ ላይቀር ተስፋ የሰጠው፣ የተስፋውን ቃልም በዘመን ፍፃሜ አንድ ልጁን በመላክ ያረጋገጠው የፍቅር መገኛ ምንጭ ልዑል አምላክ ነበር፡፡ በሰው ላይ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው የሚገልፀው መለኮታዊ ጥበቃ፣ ለሥጋዊ ምግቡ በሚያገኘው ምድራዊ በረከት፣ ከሀዘኑ ከጭንቀቱና ከፍራቻው በላይ በሚታደለው የሰላምና የመጽናናት መንፈስ የእግዚአብሔር ፍቅር በየጊዜውና በየሰዓቱ ይገለጣል፡፡ ይልቁንም ወሰን በሌለው ትዕግስቱ በኃጢአት ምክንያት ከፈቃዱ ሲጣላ ከሃሳብ ሲጋጭ የሚገኘውን ሰው ዓይኑ እንዳየች ሳይፈርድ ጆሮው እንደሰማ ሳይበይን ለንስሐ ዕድሜ መስጠቱ ሌላው ዓይነተኛ የፍቅሩ መግለጫ ነው፡፡ የእግዚአብሔርን የፍቅር ሥራ የሕያው አምላክን የፍቅር ስጦታ መዘርዘር የዝናብን ጠብታ የመቁጠር ያህል ነው፡፡

እንዲያው ነቢዩ እንዳለው ‹‹የእግዚአብሔር ቸርነት ምድርን ሞላች›› መዝ፡ 32፣5 ሐዋርያውም እንደገለፀው ‹‹ስለማይነገር ሥጦታው እግዚአብሔር ይመስገን›› 2ቆሮ 9፣15 ብሎ ማለፉ የሚቀል ይመስላል፡፡ የዚህ ድንቅ ፍቅር ባለቤት የሆነው እግዚአብሔር በባህሪው ፍቅር ነውና በአርአያው ለፈጠረው ሰው የሰጠው ሕግ የፍቅር ሕግ ነበር፡፡ የተዘረዘሩ በርካታ ህግጋት ቢኖሩም እንኳን ሕግጋት ሁሉ ፍቅረ እግዚአብሔርና እና ፍቅረ ቢፅ በተሰኙ ሁለት ሕግጋት ይጠቀለላሉ፡፡ የፍቅር አምላክ እግዚአብሔር ከሁሉ በፊት ሰዎች እርስ በርሳቸው አጥብቀው እንዲዋደዱ አዟል፡፡ ፍቅር የክርስትና ሃይማኖት መሠረት፣ የአምላክ ከሰማይ ወደ ምድር የመውረድ ምስጢር፣ የጌታ ልጆች የእምነት ማህተብ፣ የደቀመዝምርነት ልዩ ምልክት ነው፡፡ ስለሆነም ከምንም ነገር በላይ ከየትኛውም ነገር በፊት ክርስቲያኖች ሊሸከሙት የሚገባ መስቀል፣ ሊያነግቡት የሚገባ ዓርማ ሊሆን ይገባል፡፡ ፍቅር የሌለበት እምነት፣ ፍቅር የጎደለው ፀሎት፣ ፍቅር ያልቀደመው ቸርነት፣ በፍቅር ያልታጀበ አገልግሎት እንዲው ባዶ ደምሮ ደምሮ በዜሮ የማባዛት ያህል ነው፡፡

ስለዚህም ወገኖች ልብ እንበል ጌታ በነገር ሁሉ ማስተዋልን ይስጠን፡፡ ቅድሳት መጻሕፍትን ስንመረምር እንደምናገኘው እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለው ዓላማው ፍቅር ነው መኃ 2፣4 ለወደዳቸውም ሰዎች የሚያነሳው የመጀመሪያው ጥያቄ ‹‹የዮናስ ልጅ ስምዖን ሆይ ትወደኛለህን›› የሚል ነው ዮሐ 21፣16 ፡፡ የጌታ ቀዳሚ ትዕዛዙም ‹‹የኃጢአትን ብዛት ፍቅር ይሸፍናልና ከሁሉ በፊት እርስበርሳችሁ አጥብቃችው ተዋደዱ›› ይሰኛል፡፡ 1ጴ 4፣8፡፡ የዚህ ትዕዛዝ ዓላማ እርስ በርስ አጥብቆ መዋደድ ሲሆን ግቡም የኃጢአትን ብዛት መሸፈን ነው፡፡ በፍቅር የማይፈጠር ታሪክ፣ የማይለወጥ ተፈጥሮ ሕግ፣ የማይከፈል ባህር፣ የማይናድ ተራራ፣ የማይሞላ ሸለቆ፣ የማይገሰፅ ማዕበል የለም፡፡ ፍቅር ከሌለ ሁሉ ባዶ ዜሮ እንደሚሆን ሁሉ በፍቅርም ሁሉ ይሆናል፡፡ የኀጢአት ብዛትም ይሸፈናል፡፡ እንደደም የቀላው ኃጢአት እንደ ባዘቶ የሚጠራው፣ እንደ አለላ የሆነው በደል እንደ አመዳይ የሚነፃው በፍቅር ነው፡፡ ፍቅር ካለ የተናጠልም ሆነ የማኅበር ኃጢአት አይኖርም፡፡ ቢኖርም እንኳ የፍቅር ጌታ በክርስቲያኖች ኅብረት መሐል ባለው የፍቅር ሙላት የኃጢአትን ብዛት ይሸፍነዋል፡፡ ስለዚህ ክርስቲያኖች ቅደም ተከተል እንወቅ፡፡ ቃሉ እንደሚያዘን ከሁሉ በፊት አጥብቀን እንዋደድ፡፡

ብዙ ጊዜ ንፋስን እንደምንጎስም እየሆንን በከንቱ የምንባክነው ፊተኛውን ደረጃ ዘለን በ2ኛውና በ3ኛው ደረጃ ላይ ስለምንቧቸር ነው፡፡ ፍቅር ያለው ሁሉ አለውና በመጀመሪያው ደረጃ ላይ ብንፀና ተስፋዎች፣ ስጦታዎችና በረከቶችን ሁሉ ወደ እና ይወርዳሉ፡፡ ስለሆነም ቂምና በቀልን፣ ቅሬታንና ቅያሜን፣ መተቻቸትና መነቃቀፍን አስወግደን ያለጥቁረትና ያለፊት መጨማደድ በቅንነትና በየዋህነት መንፈስ አጥብቀን ልንዋደድ ይገባል፡፡ ይህ ከሆነ አፅራረ ፍቅር ሌጌዎን ወደ እርያዎቹና ወደ ባህሩ ይጣደፋል፡፡ የጦቢያና የሰንበለጥ ስላቅ የፈርኦንና የስናክሬም ዛቻ የጎልያድና የናቡከደነፆር ትምክህት እንደምናምን የሚቆጠረው በክርስቲያኖች ፍቅር ነው፡፡ በመሆኑም የፍቅር ጌታ ከሁሉ በፊት ይህንን ያዙ አለን፡፡ ፍቅርን መያዝን፣ በፍቅር መኖርን፣ በፍቅር መፅናትን፣ በፍቅር መሞትን ለሁላችን ያድለን፡፡

የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ!

መምህር ጨምር ተፈራ

የሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የስብከተ ወንጌል መምሪያ ኃላፊ

 
<< ጀምር < ወደኋላ 101 102 103 104 105 106 107 108 109 110 ወደፊት > መጨረሻ >>

ገጽ 103 ከ 111

አድራሻ

አዲስ አበባ ፤ ኢትዮጵያ

ኢ-ሜይል: aadioces@gmail.com

ድረ ገጹ ውስጥ ይፈልጉ

ሀሳበ ባሕር(የዘመን ቁጥር)

ባሕረ ሐሳብ የዘመን መቁጠሪያ

ግጻዌ