መንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም

የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ገነተ ጽጌ ቅ/ጊዮርጊስ

የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለም

የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

መንበረ ጸባዖት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል

የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ርዕሰ አድባራት መንበረ ፀሐይ እንጦጦ ማርያም

የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ምስካየ ኅዙናን መድኃኔኃለም ገዳም

የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም

የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ደብረ ጽጌ ቅድስ ኡራኤል

የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

መንበረ መንግሥት ቅ/ገብርኤል ገዳም

የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ደብረ ኃይል ራጉኤል

የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

http://www.addisababa.eotc-churches.org/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/590538kidste_mariam.jpg http://www.addisababa.eotc-churches.org/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/895720giorgis.jpg http://www.addisababa.eotc-churches.org/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/903816bole_medhaniealem.jpg http://www.addisababa.eotc-churches.org/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/683566trinity.jpg http://www.addisababa.eotc-churches.org/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/821897entoto_mariam.jpg http://www.addisababa.eotc-churches.org/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/310283meskaye_1.jpg http://www.addisababa.eotc-churches.org/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/904160BEATA_MARIAM.jpg http://www.addisababa.eotc-churches.org/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/578084urael.jpg http://www.addisababa.eotc-churches.org/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/812647gebrie_gedam.jpg http://www.addisababa.eotc-churches.org/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/681179raguel.jpg
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ የ2010 ዓ.ም የልደት በዓልን አስመልክተው መልእክት አስተላለፉ

pp009

ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በእንተ በዓለ ልደቱ ለእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ሎቱ ስብሐት!!

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!

-በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፤

-ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤

-የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤

-በሕመም ምክንያት በየፀበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤

-እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤

በልደቱ፣ ፍጻሜ የሌለው ሰላምን ያበሠረን፤ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ 

እንኳን ለብርሃነ ልደቱ በሰላም አደረሳችሁ!!

ወአልቦ ማኅለቅት ለሰላሙ፤ለሰላሙ ፍጻሜ የለውም፤(ኢሳ.9:7)

በዚህም ዓለም ይሁን በወዲያኛው ዓለም፣ በግዙፋኑም ይሁን በረቂቃኑ ፣ በኃያላኑም ይሁን በድኩማኑ፣ በሀብታሙም ይሁን በድሀው በአጠቃላይ በተንቀሳቃሹ ፍጡር ሀልዎት ውስጥ መቀጠል የሰላም አስፈላጊነት ከሌላው ጸጋ ሁሉ የላቀ ነው፣ሰላም ካለ ሌላው ሁሉ የትም አያመልጥም፤ ሰላም ካለ ድህነቱም ይቀረፋል፣ ጕድለቱም ይሟላል፣ልማቱም ይስፋፋል፣ዕድገቱም ይረጋገጣል፣ ፍትሕ ርትዕም ይሰፍናል፤ ወንድማማችነቱም ይጸናል፤ አንድነቱም ይረጋገጣል፣ ሰላም በዕለት ተዕለት ሥራችንና በምድራዊ ሕይወታችን በሚሆን ገጠመኝ ብቻ ሳይሆን ከፈጣሪ ጋር በሚኖረን ግንኙነትም ዓቢይ ትርጉም አለው፤ ለሰላም ህልውና መጠበቅ ትልቅ ስፍራ ያለው ፈጣሬ ፍጥረታት እግዚአብሔር የሰላም አምላክ ነውና ፍጡራን በሰላም እንዲኖሩ መለኮታዊ መልእክቱን ማስተላለፍ ብቻ ሳይሆን መሥዋዕትነትም ከፍሎበታል፤ ለዚህም ዋናው ማስረጃችን የአምላክ ሰው መሆንና በሰው አካል በዚህ ዓለም ተገልጾ ስለ ሰላም የሰጠው ጥልቅ ትምህርት ነው፡፡

በትምህርትም በተግባርም እንደምንገነዘበው በሰዎች ግብታዊ ድርጊትም ሆነ፣ ሆን ተብሎ በሚፈጸም ማስተዋል የጎደለው ክንዋኔ ሰላም ሊደፈርስ ይችላል፤ በአንጻሩ ሰዎች በማስተዋል፣ አርቆ በማሰብና በብዝኃ ትዕግሥት በሚመሩት ጤናማ ሕይወት ሰላም ሊፀና ሊሰፋና ወደ ላቀ ደረጃ ሊሸጋገር ይችላል፡፡

በየዓመቱ የምናከብረው የጌታችን በዓለ ልደት ይህንን ሐቅ ቊልጭ አድርጎ ያሳየናል፣የበዓሉ ታሪካዊ መነሻ እንደሚነግረን የቀደሙ ወላጆቻችን ማለትም አዳምና ሔዋን ለሕይወታቸው ጠቃሚ የሆነው ሕገ እግዚአብሔር በውል ተነግሮአቸው እያለ በጎን የመጣውን የጠላት ምክር ተቀብለውና ሆን ብለው ትእዛዙን ስለተዳፈሩ ሰላም ሊደፈርስባቸው ችሏል፡፡

በመሆኑም ያደፈረሱት ሰላም ቅጣትን አስፈርዶ ዕርቃናቸውን አስቀራቸው፤ በሐፍረት አከናነባቸው፤ መሠወር ባይችሉም መሸሸግንና መሸፋፈንን እንደ አማራጭ ዘዴ ሊጠቀሙ ሞከሩ፣ እውነተኛው ዳኛ ለምን ሰላሙን አደፈረሳችሁ ብሎ በጠየቃቸው ጊዜ ምክንያቶችን ቢደረድሩም በቀጥተኛው ሕግ ፊት ማምለጫ አላገኙም፤ ምክንያቱም ሰላምን አደፍርሰው ሞትን እንዳይጎትቱ ማስጠንቀቂያው ከበቂ በላይ በግልፅ ተነግሮአቸው ነበርና ነው፡፡

የጉዳቱ መጠን በዚህም አላበቃም፣ በእነሱ ጠንቅ ዘራቸውም  ተቀጣ፣ በምድር ላይ የሚገኙ ፍጥረታትና ምድሪቱም ራስዋ በከባድ መርገም ተቀጣች፤ በዚህም ምክንያት የሰው ሁለንተናዊ ሕይወት ዘላቂና እውነተኛ ሰላምዋ የሆነው እግዚአብሔርን አጥታ ለአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዓመታት በተሳሳተ አምልኮና በተመሰቃቀለ ህላዌ እየታመሰች፣ ሞትና መቃብርም ያለማቋረጥ እየተናጠቋት፣ እግዚአብሔር ያዘጋጀላት ብሩህ ዓለም ተዘግቶባት በጨለማው ዓለም ውስጥ ስትማቅቅ ኑራለች፤ የዚህ ሁሉ መከራ መንሥኤው አንድና አንድ ብቻ ነበር፤ እሱም የሰላሙ ኃይል እንደዋዛ ከእጅዋ ማምለጡ ነው፡፡

 የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት

ከሦስቱ አካላት አንዱ የሆነው እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ሰው ሆኖ የተወለደውና በዚህ ዓለም የተገለፀው ለሰላሙ ፍጻሜ የለውም ብሎ በቅዱሳን ነቢያቱ ያናገረውን የማይታጠፍ ቃሉን ለመፈጸም ነው፡፡

ቅዱሳን መላእክትም በጌታችን ዕለተ ልደት በቤተ ልሔም ተገኝተው እግዚአብሔርና ሰው በመገናኘታቸው ሰላም በምድር ሆነ፤ ይህም በእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ተከናወነ ብለው በመዘመር፣እረኞችም የመዝሙሩ ተጋሪ በመሆን ያሳዩት አንድነት የተነገረው ሰላም መፈጸሙን ያረጋገጠ ነበር ፡፡

በእርግጥም በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ሰላም መፈጠሩን ለመረዳት እግዚአብሔር ሰው ሆኖ ከተገለጠበት ክሥተት የበለጠ ሌላ ማረጋገጫ ሊገኝ አይችልም፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዕለተ ልደቱ እስከ መዋዕለ ዕርገቱ ድረስ በፈጸመው የቤዛነት ተግባር፣ የደፈረሰውን ሰላም እንደገና በመመለስ በሰውና በሰው፣በእግዚአብሔርና በሰው፣በመላእክትና በሰው መካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ በመናድ ሰላማችንና አንድነታችንን እውን አድርጎአል፤ ከጨለማው ዓለም ብሩህ ወደሆነው ዓለም እንደገና መልሶናል፤ ይህ እግዚአብሔር በምሕረቱ ብዛት ለሰው ልጅ ያጎናጸፈው ትልቁ፣ ዘላቂውና ዘላለማዊው ሰላም ነው፤ እሱም እኔ  ሰላሜን እሰጣችኋሁ፤ እኔ የምሰጠው ሰላም ዓለም እንደሚሰጠው ያለ አይደለም  ብሎ የተናገረለት ሰማያዊ፣ ዘላለማዊና ሳይቀለበስ ለዘላለሙ ጸንቶ የሚኖረው፣ ከእርሱና ከፍጡራን ሁሉ ጋር የሚሆነውና መጨረሻ የሌለው  ሰላም ይህ በልደቱ ተጀምሮ በዳግም ምጽአቱ የሚደመደመው ታላቁ ሰላም ነው ፡፡

ይሁን እንጂ በምድርም ቢሆን ሰው ዛሬውኑ አዳምጦ፣ አስተውሎ፣ አምኖና ተቀብሎ በተግባር ቢያውለው ጌታችን የሰላም ትምህርቱን ለክርክር በማይዳርግ መልኩ ሰጥቶአል፤ እርሱም  ‹‹ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ  እናንተም እንደዚሁ አድርጉላቸው፤ በራስህ ላይ ሊደረግብህ የማትሻውን በባልንጀራህ ላይ አታድርግ፤ ባልንጀራህን እንደራስህ አድርገህ ውደድ›› የሚለው እውነተኛ የሰላም መንገድ ነው፤ ዛሬም ይህን ቃሉን ተቀብለን በተግባር ብንፈጽም ሰላማችን አስተማማኝና ዘላቂ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት፡-

ሰላም ማለት የእግዚአብሔር ሕግ ማለት ነው፤ ሰላምን የፈጠረ፤ ከማንም አስቀድሞ ስለ ሰላም ያስተማረና አሰምቶ የተናገረ፤ ደጋግሞም ያስጠነቀቀ እግዚአብሔር ነው፤ቃሌን ብታደምጥ ብትጠብቀውም ሰላምህ እንደማያቋርጥ ወንዝ ይጎርፋል ያለ እርሱ ነው ፡፡

ይህም ማለት ዘላቂና ፍጹም ሰላም ያለው በእግዚአብሔር ሕግ ውስጥ መሆኑን ያሳያል፤ ይህንን ሕገ ሰላም አውቀን በታላቅ አክብሮትና ምስጋና ስንቀበለው ሰላማችን ዘላቂና አስተማማኝ ይሆናል ማለት ነው፤ ዘላቂና ፍጹም የሆነ የእግዚአብሔር ሰላም በአንድ አጭር ዐረፍተ ነገር ባልንጀራህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ›› ተብሎ ተነግሮናል፡፡

ይህ ዓቢይና መለኮታዊ የሰላም ሕግ ከተከበረ መለያየት፣ መጣላት፣ መጨካከን፣ መገዳደል፣ በየት መግቢያ ያገኛል? እግዚአብሔር የሚፈልገው ሰላም ምን ዓይነት እንደሆነ መመዘኛውና መለኪያው እኛ ራሳችንን የምንወደው ያህል ወንድሞቻችንንና እኅቶቻችንን መውደድ ነው፤ በዚህ ፍጹምና አምላካዊ ሕግ በእግዚአብሔር መልክና አምሳል የተፈጠረውን ሰው ሁሉ እንደራሳችን አድርገን እንድንወድ ታዘናል፤ እኛም አምነን ተቀብለናል፤ ይህንን የእግዚአብሔር ድምፅ ያልሰማ ሰው በሀገራችን በኢትዮጵያም ሆነ በሌላው ክፍለ ዓለም ይኖራል ብለን አንገምትም፤ነገር ግን የቀደሙ ወላጆቻችን የእግዚአብሔርን ድምፅ ወደጎን ትተው በመጓዛቸው እንደተጎዱ፣ ዛሬም የሰው ልጅ ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ የሚለውን ድምፅ ቸል በማለት አጥፍቶ በሚጠፋ ቊሳቊስ እየተጣላ የሰላሙን ጭላንጭል በገዛ ራሱ እያጨለመው ይገኛል፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት

ሰላምን ለመጎናጸፍ ሁለት ዐረፍተ ነገሮችን መቀበልና ዘወትር ስለነሱ መዘመር በቂያችን ነው፣ እነርሱም እግዚአብሔር አምላክህን በሁለመናህ ውደድ፤ ባልንጀራህንም እንደራስህ አድርገህ ውደድ የሚሉት ናቸው፡፡

ይህች ፍቅር የእግዚአብሔር ጸጋ ሆና የተሰጠችን፣ ሌላ አማራጭና ተፎካካሪ የሌላት ፣ ኅሊናን ሁሉ የምትረታ ናት፣ምንጩ እግዚአብሔር የሆነ የሰላምና  የፍቅር ኃይል  ድንበር ፣ ወንዝ ፣ ቋንቋ  አይገድበውም፤ በመሆኑም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሙሉእ ሰላምን የሚሰጠው እግዚአብሔር ስለሆነ፣ አሁኑኑ እግዚአብሔርን ያድምጥ፤ ያዳመጠ ዕለታ ‹‹ወንድምህን እንደራስህ አድርገህ ውደድ፣ ወንድምህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ፣ ወንድምህን እንደራስህ አድርገህ ውደድ›› የሚል ቃል በተደጋጋሚ ከአምላኩ አንደበት ይሰማል፣ እርሱን ተቀብሎ በተግባር ሲያውል እግዚአብሔር አምላክህን በሁለመናህ ውደድ የሚለው ፍቅር በሕይወቱ ይገለጻል፤ በእርሱም ፍጹም ሰላም ያገኛል፡፡ ከዚህ አኳያ በዓለ ልደቱን ስናከብር እርሱ እንደራራልን እኛም የእርሱን ፈለግ ተከትለን የተራቡትን፣ የተጠሙትን፣ የታረዙትንና የተፈናቀሉትን በመርዳት እንዲሁም ቀኑ የሁሉም ወገን የደስታ ቀን እንዲሆን በማድረግ ልናከብር ይገባል፡፡

በመጨረሻም

ጅብ በቀደደው እንደተባለው ዘላቂ የሆነ የጋራ ጥቅማችንን ሳናይ በምንፈጥረው ስሜታዊ ክፍተት ተጠቅመው ታላቅነታችንንና ዕድገታችንን የማይሹ ኃይሎች ከሕዳሴው አጀንዳችን እንዳያናውጡን ኢትዮያውያን የሆን ሁላችን፣ ከሃይማኖታችን ያገኘነውን ቅዱሱና ሰላማዊው የአንድነት ሀብታችንን ጠብቀን፣ ቂምንና በቀልን አርቀን የውስጣችንን ክፍተት ራሳችን በራሳችን አርመን በአንድነት በሰላምና ፍጹም በሆነ ወንድማዊ ፍቅር ቀጥ ብለን በመቆም ወደፊት እንድንቀጥል በእግዚአብሔር ስም መንፈሳዊመልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

መልካም የልደት በዓል ያድርግልን

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይባርክ ይቀድስ፡፡

‹‹ወስብሐት ለእግዚአብሔር››

አሜን

አባ ማትያስ ቀዳማዊ፣

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣

ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣

ታኅሣሥ ፳ ቀን ፳፻ወ ዓ.ም

አዲስ አበባ ኢትዮጵያ ፤

 

 
"ኖላዊሆሙ ለእስራኤል አጽምእ"(የእስራኤል ጠባቂ ሆይ አድምጥ)

                                                                                                                      በመ/ር ሣህሉ አድማሱ

4521

በቤተክርስቲያናችን የቃለ እግዚአብሔር አሰጣጥ መሠረት ከብርሃን ቀጥሎ ያለው ሳምንት ኖላዊ ተብሎ ተሰይሟል፡፡

ኖላዊ ተብሎ  በሚጠራው ሰንበት "ኖላዊ  ዘመጽአ…" የሚለው የቅዱስ ያሬድ የዜማ ድርሰት በሌሊት  የአገልግሎት ክፍለ ሰዓት በሊቃውንቱ ሲዘመር ያድራል፡፡ በጧቱ በሥርዓተ  ቅዳሴ ወቅት (ዕብ.13÷16)፣ (1ጴ 2÷21)፣ (የሐ.10÷36-43 በዲያቆናትና  በካህኑ  በንባብ ይቀርባል፡፡ የእስራኤል ጠባቂ ሆይ አድምጥ፣ዮሴፍን እንደመንጋ  የምትመራ፣ በኪሩቤል  ላይ የምትቀመጥ ተገለጥ የሚለው የዳዊት መዝሙር (መዝ 79÷1) በዲያቆኑ በዜማ ይቀርባል፡፡ (ዮሐ 10÷1-22) በካህኑ በዜማ ይቀርባል፡፡ ቃሉም እንዲህ ይነበባል፡፡ 

"አማን አማን  እብለክሙ ዘኢቦአ እነተ  አንቀጽ ውስተ አጸደ አባግዕ ወአርገ እንተካልእ ገጽሰራቂ ወፈያት ወጉህልያ ውእቱ"

"እውነት እውነት እላችኋለሁ ወደ በጎች በረት በበሩ የማይገባ በሌላ መንገድ ግን የሚወጣ እርሱ ሌባ ወንበዴም ነው፡፡ በበሩ የሚገባ ግን የበጎች  እረኛ ነው፡፡  ለእርሱ  በረኛው  ይከፍትለታል፡፡ በጎቹም ድምጹን ይሰሙታል፡፡የራሱንም በጎች በየስማቸው ጠርቶ  ይወስዳቸዋል፡ ፡የራሱንም ሁሉ ካወጣቸው በኋላ በፊታቸው ይሄዳል፡፡ በጎቹም ድምፁን ያውቃሉና ይከተሉታል፡፡ ከሌላው ግን ይሸሻሉ እንጂ አይከተሉትም፡፡ የሌሎችን ድምፅ  አያውቁምና፡፡ .. እኔ የበጎች  በር  ነኝ….በሩ እኔ ነኝ በእኔ የሚገባ  ይድናል፡፡

….መልካም እረኛ እኔ ነኝ፡፡ መልካም እረኛ ነፍሱን ስለበጎቹ ያኖራል፡፡ እረኛ ያልሆነው በጎቹ የእርሱ ያልሆኑ ሞያተኛ ግን ተኩላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ  ይሸሻል፡፡

በግ

በግ ሥጋው  ለመስዋዕትነትና ለምግብ፣ ጠጉሩና ቆዳው ደግሞ ለልብስ  የሚሆን  የዋህ የቤት እንስሳ ነው (ዘፍ 4÷2) (ዘሌ 22÷19) (ዘፀ 14÷13) በግ በተለይ  ለፋሲካ መስዋዕት  ይታረድ ነበር (ዘፀ 12÷3) ስለዚህ ክርስቶስ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአበሔር  በግ ተብሏል፡፡ (ዮሐ1÷29) (ራዕ 5÷6)በግ ንጹሕና የማይጎዳ የዋህ እንስሳ ስለሆነ ሐሰተኞች  የዋህ  ለመምሰል  የበግ  ለምድ  በሚለብሱ  ተመስለዋል፡፡ (ማቴ 7÷15)በጎች ክርስቶስን የሚከተሉ ምዕመናን ምሳሌ ናቸው፡፡(ማቴ 25÷33)

እረኛ

 በጎችንና ፍየሎችን ከብቶችንም የሚያሰማራ እረኛ ተብሎ ይጠራል፡፡ (መዝ 23÷2)እረኛ  የጠፋውን  ይፈልጋል፡፡ (ሉቃ 15÷3) ከአውሬዎችም ይጠብቃል(1ሳሙ 17÷34)

እረኛ ኃላፊነት ላለባቸው ሁሉ ምሳሌ ነውና፣ ሕዝብን የማይጠብቁ ባለስልጣኖች ከባድ  ፍርድ  ይጠብቃቸዋል፡፡ (ኤር23÷1)፣ (ሕዝ34÷1)

በበሉይ ኪዳን ስለ እግዚአብሔር እረኝነት የተነገረው ሁሉ በአዲስ ኪዳን ለክርስቶስ  ተነግሯል፡፡ ይህም ክርስቶስ ራሱ እግዚአብሔር መሆኑን ያመለክታል፡፡ ኢየሱስ ፈሪሳውያን ዕውር መሆናቸውን ተናግሮ እንደጨረሰ ስለመልካም እረኛ ማስተማር ጀመረ፡፡ በብሉይ ኪዳን እንደተጻፈው የአይሁድ መሪዎች የእስራኤል ጠባቂዎች እረኞች ናቸው፡፡

ይሁን እንጂ መሪዎች ይህን ሀላፊነት መወጣት አልቻሉም፡፡ ዕውሮችና ምንም ነገር የማያውቁ ሆኑ (ኢሳ 56÷9)ሐሰተኞች፣ በበጎች በር የማይገቡ፣ ሌቦችና ወንበዴዎች ሆኑ፡፡

እውነተኛ እረኛ የሆነው ከርስቶስ ሁል ጊዜ በበሩ  ይገባል፡፡ በብሉይ ኪዳን እራሱ እግዚአብሔር የእስራኤል እረኛ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ (መዝ 23÷1) ፣ (ሕዝ34÷15) ኢየሱስ ክርስቶስ እረኛችን ነው፡፡ እርሱም ከእርሱ በታች ሌሎች እረኞችን  ሾሟል፡፡ (የሐ 20፣17)ክርስቶስ ሕይወቱን ለበጎች አሳልፎ የሰጠ መልካም እረኛ ነው፡፡

ቅጥረኛ እረኛ ግን ተኩላ ሲመጣ በጎቹን ጥሎ ይሸሻል፡፡ በየትኛውም ዘመን ከቤተክርስቲያን መሪዎች መካከል ቅጥረኛ የሆኑ እረኞች አሉ፡፡ እነዚህ እረኞች መንጋውን  አያስቀድሙም፡፡ አንድ ችግር በመጣ ጊዜ መንጋውን በትነው  ይሸሻሉ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በጎቹን ያውቃል ፣ ደግሞም በጎቹን ይወዳል፡፡ በመሆኑም ስለበጎቹ ሕይወቱን አሳልፎ ሰጥቷል፡፡

 

 

 
“እውነተኛው የዓለም ብርሃን”

                                                                                                                               በመምህር ኪዱ ዜናዊ
ብርሃን÷ ብርሃን የጨለማ ተቃራኒ ነው፤ ለዚያም ነው ብርሃን የሌለበት ጨለማ ተብሎ የሚጠራው። ጨለማ መኖሩ የሚታወቀው ብርሃን ሳይኖር ሲቀር ነው። ብርሃን በሁለት መልኩ ልንገልጸው እንችላለን÷ ውጫዊ(ዓለማዊ) እና መንፈሳዊ(ውስጣዊ)፤ የመጀመርያው ከተፈጥሮአዊው(ፀሐይ) ወይም ከሰው ሰራሽ የሚገኝ ሲሆን ያንን ብርሃን ወደ ዓይናችን ሲያንጸባርቅ ነገሮችን ማየት እንችላለን፤ ዓይናችን ያ ብርሃን ካላገኘ ግን ጨለማ ነው ምንም ማየት አይችልም። ሁለተኛው ግን ከመጀመርያው በእጅጉ የተለየ የረቀቀ ብርሃን ነው÷ መንፈሳዊ ብርሃን፤ ውስጣዊ ብርሃን። እግዚአብሔር መንፈስም ብርሃንም ነው(ዮሐ 4:24፤ 1ዮሐ 1:5) እግዚአብሔር በአማኞቹ ልብም ያበራል፤ እንዲህ ስንል ግን በመካከላቸው የሚጋርድ ነገር(ኃጢአት) ከሌለ ነው። ምክንያቱም አምላክ ኃጢአትን ይጸየፋልና።
እንደ ቤተ- ክርስቲያናችን ሥርዓትና ቀኖና ከገና በፊት ያሉት ሦስት ሰናብት ማለትም ስብከት፣ ብርሃን፣ ኖላዊ አንድላይ ዘመነ ስብከት ተብለው ይጠራሉ፡፡ የዘመነ ስብከት ሁለተኛ እሁድ ብርሃን ይባላል።ሌሊቱን ከቅዱስ ያሬድ  መዝሙር    «አቅዲሙ ነገረ በኦሪት» በኦሪት መናገርን አስቀደመ  ብለው በመጀመር በሊቃውንቱ ሲዘመር በዜማ አምላክን ሲወደስና ሲመሰገን ካደረ በኋላ ጧት ደግሞ በሥርዓተ ቅዳሴ  (ሮሜ.13፥11-ፍጻሜ)፣ (1ዮሐ.1፥1-ፍጻሜ)፣ (የሐዋ.26፥12-19) በዲያቆናት እና በካህናት ይነበባሉ። (መዝ.42፥3) በዲያቆኑ በዜማ ይቀርባል፡፡ (ዮሐ.1፥1-19) በካህኑ  ይነበባል እንዲሁም የሊቁ የአትናቴዎስ የምስጋና ጸሎት ይደርሳል ፡፡ እነዚህም ሁሉ ስለ ብርሃኑ ሰፋ ያለ መልእክት ያላቸው ከብሉያትና ከሐዲሳት እንዲሁም ከሊቃውንቱ መጻሕፍት የተውጣጡ ብርሃንነቱን የሚመሰክሩ ናቸው ፡፡
ይህ ሳምንት ብርሃን ተብሎ መጠራቱ ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት የነበሩ ሰዎች በመንፈሳዊ ጨለማ ተውጠው ይህንን ጨለማ የሚያስወግድ መንፈሳዊ ብርሃን በመሻት አምላክን ሲማጸኑት እንደነበሩ ለማዘከር፤ በአሁን ሰዓት ያሉ አማንያንም ብርሃን መጥቶ ጨለማን በማስወገድ ስለታደጋቸው ለማመስገን ላላመኑትና ላላወቁት ደግሞ  <እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ>  እንዳለው በዓለም ውስጥ ብርሃን ሆኖው ብርሃኑን እያመሰገኑ ያ ብርሃን መግለጥና ለዓለም ሁሉ መስበክ ነው።
ቅዱሳን ነቢያት ሰው ሁሉ በጨለማ ውስጥ መሆኑን (መኖሩን) አውቀው ተረድተው ይህንን ጨለማ ለማስወገድ ደግሞ ብርሃን እንደሚያስፈልግ በማመን የብርሃን ባለቤት ለሆኖው  አምላካችንን ብርሃን እንዲልክላቸው የዘወትር ልመናቸውና ጸሎታቸው እንደነበረና የነፍሳቸውን ብርሃን ይመጣል ብለው መስበካቸውን  ከጽሑፋቸው አይተን እንረዳለን፤ ለሰው ልጅ ድኅነት ከጠበቁባቸው እና ከገለጡባቸው መንገዶችም አንዱ ይህንን ብርሃን እንዲላክላቸው ነበር፡፡ ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት በዘመነ ብሉይ÷ ደዌ-ሥጋ፣ ደዌ- ነፍስ የፀናበት፣ ለሰው ሁሉ አስጨናቂ ዘመን የሆነበት፣ሁሉም  ሰው ብርሃን ከሆነው አምላኩ ርቆ በጭንቅ፣ በመከራና በጨለማ ውስጥ በመኖሩ ተስፋ ቢስ ሆኖ ስለነበር ዘመኑን « ዘመነ-ጨለማ» ብለው በመግለጥ ይህንን ጨለማ  አስወግዶ ወደ ብርሃን የሚቀይር በጨለማ የሚያበራ ብርሃን እንዲላክላቸውና ከብርሃን የተገኘ እውነተኛ ብርሃን፤አማናዊ ብርሃን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  እንዲመጣ ዘወትር ሲጸልዩ ነበር፡፡ መዝሙረኛውም ያን ብርሃን መሻቱን እንዲህ ሲል በመዝሙሩ ጸልዮአል÷
<ፈኑ ብርሃነከ ወጽድቀከ እማንቱ ይምርሐኒ ወይሰዳኒ ደብረ መቅደስከ  ወውስተ አብያቲከ እግዚኦ> /መዝ. 42.3/አቤቱ ብርሃንህንና እውነትህን (ጽድቅህን) ላክ እነርሱ ይምሩኝ ወደ መቅደስህ ተራራና ወደ ማደሪያህ ይወሰዱኝ፣ 
ብርሃን የሆነ፣ጽድቅ የሆነ፣ እውነት የሆነውን ቅዱስ ልጅህን(ወልድን) ክንድህን ልከህ ጨለማ ሆኖ የጋረደንና ካንተ የለየን ኃጢአታችን አስወግዶ ከአንተ አስታርቆ ወደ አንተ ይውሰደን ሲል ነው።  የዚህ ሁሉ ትንቢትና ጸሎት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  በአባቱ ተልኮና በፈቃዱ ወደዚህ ዓለም በመምጣት ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ በተዋህዶ ፍጹም አምላክና ሰው ሆኖ በዓለም ሲያስተምር  «እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ» /ዮሐ. 8.12/ በማለት ብርሃንነቱን አረጋግጧል፤ በመቀጠልም እርሱን የሚከተል ሁሉም ያንን ብርሃን እንደሚያገኝ እንዲህ በማለት ተናግሯል‹‹ እኔን የሚከተል ሁሉ የሕይወት ብርሃን ያገኛል በጨለማም አይመላለስም››(ዮሐ 8:12)። ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ሁሉ ሕይወት የሆነች ብርሃን ገልጧል፤ ብርሃን መሆኑን ደቀመዛሙርቱም ስለ  ብርሃንነቱ እንዲህ በማለት መስከሯል «ሕይወት በእርሱ ነበረ፣ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረ፤ ብርሃንም በጨለማ ያበራል፤ ጨለማም አላሸነፈውም» /ዮሐ. 1.4-5/። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጨለማ ያላሸነፈው ዘወትር የሚያበራ  እውነተኛ ብርሃን ነው። ሊቃውንትም ‹ዘዘልፈ ያበርህ፣ብርሃን ዘበአማን› ሁሉ ጊዜ የሚያበራ እውነተኛ ብርሃን ‹ዘእንተ ውስጥ አይነነ አብራህከ ወጽልመተ ሐሊናነ፣ብርሃነ_ፍጹማን ወልደ አምላክ ሕያው› የሕሊናችንን ጽልመት ያበራ፣ ዓይነ ልቡናችንን የገለጠው፣ የሕያው አምላክ ልጅ የፍጹማን ብርሃን ብለውታል። ዮሐንስም ስለዚህ ብርሃን ሲመሰክር ለሰው ሁሉ የሚያበራ እውነተኛ ብርሃን ወደ ዓለም መጣ ሲል፣ ቅዱስ ጴጥሮስም ይህ ብርሃን በልቡናችን ውስጥ የሚያበራ ብርሃን ነው ብሎታል(1ኛጴጥ 1:19)።
ቅዱስ ጳውሎስም መጀመርያ በብርሃን የነበረ እንኳ ቢመስለውም ያ ብርሃን ሳይበራለት በጨለማ ሆኖ ይህንን ብርሃን ለማጥፋት የብርሃን ልጆቸና ብርሃን እያሳደደ ሳለ ጌታችንም ትጋቱንና ቅንነቱን  በመመልከት ጌታችን በሚያንፀባርቅ ብርሃን አምሳል እንደተገለጠበት ተናግሯል፡፡ « በመንገድ ሳለሁ እኩለ ቀን ሲሆን በዙሪያዬና ከኔ ጋር በሄዱት ዙሪያ ከፀሐይ ብሩህነት የበለጠ ብርሃን ከሰማይ ሲበራ አየሁ … አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ ” አለኝ(የሐዋ 26:13_15) ቅዱስ ጳውሎስ ያ ብርሃን ከበራለት በኋላ ጨለማ ከእርሱ ውስጥ ስፍራ ስላላገኘ ብርሃንነቱን ለማወጅ ተሯሩጧል፤ ሌሎችም ሲያሰተምር እርሱንም ራሱ ጨምሮ እንደህ ሲል ተናግሯል ‹‹ቀድሞ ጨለማ ነበራችሁና፥ አሁን ግን በጌታ ብርሃን ናችሁ፤ የብርሃኑ ፍሬ በበጎነትና በጽድቅ በእውነትም ሁሉ ነውና ለጌታ ደስ የሚያሰኘውን እየመረመራችሁ፥ እንደ ብርሃን ልጆች ተመላለሱ፤ፍሬም ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋር አትተባበሩ፥ ይልቁን ግለጡት እንጂ፥ እነርሱ በስውር ስለሚያደርጉት መናገር እንኳ ነውር ነውና፤ ሁሉ ግን በብርሃን ሲገለጥ ይታያል፤ የሚታየው ሁሉ ብርሃን ነውና።
ስለዚህ አንተ የምትተኛ ንቃ ከሙታንም ተነሣ ክርስቶስም ያበራልሃል ይላል›› (ኤፌ 5:8-14)። ክርስቶስ በአህዛብም ብርሃን እንደሆነ ቀድሞዉኑ ተወስኖ ነበር፤ (ኢሳ 49:6)‹…እስከ ምድር ዳር ድረስ መድኃኒት ትሆን ዘንድ ለአህዛብ ብርሃን አድርጌ ሰጥቼሃለሁ› ይላል። በጨለማ የተጓዘ እንቀፋት ሳይመታው አይቀርም፣ ክርስቶስ ግን ይህንን ጨለማ በማስወገድ ብርሃን በመሆን ከእንቅፋትም ከመሰናክልም ሊያድን መጥቷል፤ እንቅፋቱንም ያሳያል። ስለዚህ ከእንቅፋትም ከውድቀትም ለመዳን በዚህ ብርሃን መራመድ ይገባል። እመኑ በብርሃኑ ወአንሰውስዉ እንዘ ብክሙ ብርሃን እንዳለው ሊቁ፤ በብርሃኑ አምነን በብርሃን እንመላለስ። በራሳችን ካልራቅን ጨለማ ካልመረጥን እርሱ ይወደናል ስለ ወደደን ነው  ሳያዳላ ስለ ሁሉም ሰው ወደ ዓለም የመጣ‹ ብርሃን ዘበአማን ዘያበርህ ለኲሉ ሰብእ ለእለ ይነብሩ ውስተ ዓለም በእንተ ፍቅረ ሰብእ መጻእከ ውስተ ዓለም ወኲሉ ፍጥረት ተፈስሃ በምጽአትከ› ሁሉም ፍጡር የተደሰተብህ፣ ሰውን ወደህ ወደዚህ ዓለም የመጣህ፣ በዓለም ውስጥ ላለ ሁሉ ሰው የሚያበራ እውነተኛ ብርሃን ነህ ተብሏል። ታድያ እኛስ በመምጣቱ ደስተኞች ነን? ያለ እርሱስ በጨለማ ውስጥ እንደምንኖር ተገንዝበናል?
በዘመነ ኦሪት ለነበሩ ሰዎች እርሱ ራሱ የፈጠራት ፀሐይ ከእነርሱ አልጠፋችም ነበር አሁንም አለች እርሷ ለሁሉም ዓለም የፀጋ ስጦታ ናት፤ነገር ግን በመንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ ሆኖው ብርሃንህን ላክልን ሲሉ የነበረ አሁን በግዙፍ ዓይናችን የምናያት የምንመለከታት ፀሐይ የምትሰጠው ብርሃን አጥተው አይደለም፣ የውስጥን ጨለማ ድንቁርናና ኃጢአትን አስወግዶ ውስጣዊ ሕሊናን በማብራት ያለምንም እንከን አምላካችንን የምናይበትና የምንከተልበት መንፈሳዊ ዓይናችን ሊያበራ የሚችል አማናዊ ብርሃን ፈልገው ነው እንጂ፤ አሁንም እኛ የእውራን ዓይንና አእምሮ የሚገላልጠውን አማናዊ ብርሃን እንጋብዘው፤ እንድያውም እርሱ በበራችን ሆኖ እያንኳኳ ነው እንክፈትለት (ራእ 3:20)፤ እነዚያን ሰዎች ሲለምኑ ነበር እኛ ደግሞ እየተለመንን ነው፤ አንድ ቀን ጌታችን ሐዋርያትን ሲያነጋግራቸው ብዙዎች ለማየት፣ ለመስማት፣ ተመኝተው አላዩም አልሰሙምም እናንተ ግን ብፁአን ናችሁ፤ ዓይናችሁም አይቷል ጆሮአችሁም ሰምተዋል ሲል ዕድለኞች መሆናቸውን መስክሯል። ዮሐንስም እኛም በዓይናችን አይተናል እንመሰክርማለን ብሏል። ውድ አንባብያን ሆይ! እኛም ሁላችን በዚህ ብርሃን አምነን በብርሃኑ ከተመላለስን ለእኛ ብሎ ነው የመጣና የዚህ ክብርና ብርሃን ባለቤቶች ነን። በዚህ ዓለም የምናገኘው የፀሐይ ብርሃን ከሁሉም ዓለም በጋራ ነው የምንጠቀመው ውስጣዊ ማንነታችንም አይደለም አይገልጽምም፤ የሚያስደንቀው ግን የእግዚአብሔር ቸርንት ነው፤ ምክንያቱም ያ ብርሃን ለሚያምኑት ሆነ ለማያምኑት፤ ለጠላቶቹም ሆነ ለወዳጆቹም በእኩል መስጠቱ ነው፤ ሙሉ በሙሉ ባይሆንም ቀኑን በማፈራረቅ ለዓለም ስታበራ የቆየች ፀሐይ እንደ ሌሎቹ ፍጡራን አንድ ቀን ማለፍዋ ስለማይቀር የምትሰጠው ብርሃን የተፈራረቀና ውጫዊ ብርሃን  ቢሆንም እንኳ እሱም ቀጣይነት እንደሌለው የተረጋገጠ ነው፡፡  ስለዚህ ብርሃን ከሚጠሉና ጨለማን ከመረጡ ሰዎች መለየት አለብን፤ ከጨለማው ዓለምና አስተሳሰብ ወጥተን በፈጠራት ፀሐይ ዓለምን ያበራ እርሱ ራሱ ብርሃን በመሆን ደግሞ ውጫዊውንና ውሰጣዊውን የሚያበራ የሥጋና የነፍስ ብርሃን የሆነ የሕይወት ብርሃን እንያዝ እንከተል <የመዳን ቀን አሁን ነው> እንዳለው ሐዋርያው ከዓለማዊ አስተሳሰብ ወጥተን ወደመንፈሳዊና ዘላለማዊ ሕይወት ግዜው ሳይመሽ አሁን ተሎ ብለን  እንግባ፡፡ ሌላ ጊዜ አንጠብቅ በሆነ አጋጠሚ ሳንዘጋጅ ከዚህ ዓለም ከተለየን የኛ ጊዜ እሱነውና በጸጸት ሰለማይመለስ፤ ከሁሉም ነገር አስቀድማችሁ መንግስቱንና ጽድቁን ፈልጉ እንዳለን ጌታችን ቃሉን አክብረን ተዘጋጅተን እንጠብቀው። ይህንን ማድረጋችን ከመብላት፣ ከመልበስ፣ ከመስራትና ከትዳር አይከለክለንም፤ ከኃጢአትና ሥርዓት አልባ ከሆነ ዓለማዊ ምኞት እንጂ። ቅዱስ ጳውሎስም እንዲህ ብሎ እየመከረን ነው<ከእንቅልፍ የምትነሡበት ሰዓት አሁን እንደ ደረሰ ዘመኑን እወቁ፤ ካመንንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን ዛሬ ወደ እኛ ቀርቦአልና። ሌሊቱ አልፎአል፥ ቀኑም ቀርቦአል። እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር እንልበስ። በቀን እንደምንሆን በአገባብ እንመላለስ፤ በዘፈንና በስካር አይሁን፥ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፥ በክርክርና በቅናት አይሁን፤ ነገር ግን ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት፤ ምኞቱንም እንዲፈጽም ለሥጋ አታስቡ>።(ሮሜ 13:11-14)። በእርሱ ዘንድ ጨለማ የለም ሁሌም ብርሃን ነው፡፡ ‹‹ከእንግዲህም ሌሊት አይሆንም ጌታ አምላክም በእነርሱ ላይ ያበራላቸዋልና የመብራት ብርሃንና የፀሐይ ብርሃን አያስፈልጋቸውም፤ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ይነግሳሉ››(ራእ 22፡5)፡፡ ያ ብርሃንም ራሱ መድኃኔዓለም ነው፤ «ለከተማይቱም የእግዚአብሔር ክብር ስለሚያበራላት መብራትዋም በጉ ስለ ሆነ ፀሐይ ወይም ጨረቃ እንዲያበሩላት አያስፈልጋትም»(ራእ 21:13)፡፡ ውድ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች  በእውነት ይህንን  ክብርና ብርሃን ሊያመልጠን አይገባም፤ በዚህ ብርሃን   ከብርሃን አባትና ብርሃን ከሆነው ከጌታችን ከመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱሳኑምጋር ለዘላለም ለመኖር በብርሃኑ አምነን ከብርሃንና ከብርሃን ልጆች ቅዱሳን ጋር አሁን በትንሳኤ ልቡና በአብ ቀኝ እንቀመጥ (ቈላ3:1-3፤ ኤፌ2:6-7)። በብርሃኑ ልቡናችንና ሁለንተናችንን ያብራ !!!
   ወስብሃት ለእግዚአብሔር አሜን!
                     

 
<< ጀምር < ወደኋላ 1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 ወደፊት > መጨረሻ >>

ገጽ 3 ከ 111

አድራሻ

አዲስ አበባ ፤ ኢትዮጵያ

ኢ-ሜይል: aadioces@gmail.com

ድረ ገጹ ውስጥ ይፈልጉ

ሀሳበ ባሕር(የዘመን ቁጥር)

ባሕረ ሐሳብ የዘመን መቁጠሪያ

ግጻዌ